በካርቱሙ ተቃውሞ የሴቶች ሚና, "በካርቱም ሴቶች ለተቃውሞ እንዲህ በነቂስ ወጥተው ያየሁት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው"

የፎቶው ባለመብት, AFP
በሱዳን ካርቱም የጀግኒት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ማህበር ሊቀመንበር የሆኑት አስቴር ጌታሁን ነዋሪነታቸው በካርቱም አቡሃማማ የተባለ ስፍራ ነው።
“ሴቶች እንዲህ በነቂስ ወጥተው የተቃውሞ ድምፃቸውን ሲያሰሙ ያየሁት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው” ይላሉ።
እኝህ ነዋሪ እንደሚሉት በርካታ ሴቶች "ፍርድ እንፈልጋለን፣ እንዲወርድ እንፈልጋለን ፣ ነፃነት እንፈልጋለን” በማለት አደባባይ ወጥተው በጣታቸው የድል (V) ምልክት እያሳዩ፣ እያጨበጨቡ በድፍረት በየአደባባዩ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል፤ ደስታቸውንም እየገለፁ ነው።
በሃገሪቱ ከዚህ ቀደም በነበሩት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች በሃይማኖትና ሌሎች ምክንያቶች የሴቶች ተሳትፎ እምብዛም አልነበረም ያሉት ነዋሪዋ “ አሁን እየተማሩና የማህበረሰቡ አስተሳሰብ እየተለወጠ ሲመጣ ግንባር ቀደም ሆነው ተገኝተዋል” ብለዋል።
በአብዛኛው ሰልፉን ሲመሩት የነበሩት ሴቶች ናቸው የሚሉት ነዋሪዋ ወንዶችም ከኋላ በመሆን በሕብረትና በሰላማዊ መንገድ ድምፃቸውን ሲያሰሙ እንደነበር ገልፀውልናል።
"ሴቶቹ ለውጥ እንዲመጣ እንደጮኹት ሁሉ አሁንም ለውጥን አጥብቀው ይሻሉ።" ሲሉም ያክላሉ።
አሁን ለታየው ለውጥም የሴቶቹ ሚና ከፍተኛ እንደነበር የታዘቡትን አካፍለውናል።


















