
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የምስሉ መግለጫ, የበረራ አስተናጋጆች ሐዘናቸውን ሲገልጡየኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 መጋቢት 1/2011
ዓ.ም ጠዋት 2፡38 ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ለሚያደርገው በረራ ጉዞ በጀመረ ጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ወድቆ ተከስክሷል። በአደጋው
የበረራ ሠራተኞችን ጨምሮ 157 ግለሰቦች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
አደጋው በመላው ዓለም ድንጋጤን የፈጠረና ያሳዘነ ነበር። ታዲያ በረራ የዘወትር ሥራቸው
ለሆነው የበረራ አስተናጋጆች ከአደጋው በኋላ በነበራቸው በረራ ምን ተሰምቷቸው ነበር?
ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች የበረራ አስተናጋጅ ስለአደጋው የሰማችው ቤት ውስጥ ከቤተሰብ
ጋር ተሰብስበው እየተጫወቱ እንደነበር ታስታውሳለች። ከዚያም ድንገት ስልኳ አቃጨለ "ተርፈሻል?" ለማለት ከጓደኛዋ
የተደወለ ስልክ ነበር። የሰማችውም ያኔ ነው። "በፍፁም ላምን አልቻልኩም ነበር " ትላለች። ጠቅላይ ሚኒስትር
ዐብይ የሐዘን መግለጫ ሲያወጡ የሚወራው ሁሉ እርግጠኛ መሆኑን እንዳረጋገጠች ትናገራለች።
ያው የሥራ ጉዳይ ነውና ይህች የበረራ አስተናጋጅ አደጋው በተፈጠረ ዕለት ማታ ወደ ታይላንድ፣ ባንኮክ በረራ ነበራት። ይሁን
እንጂ ቤተሰቦቿ እንዳትሄድ አጥብቀው ተማፅነዋት እንደነበር ታስታውሳለች። "እናቴም፣ አያቴም፣ ሁሉም ዛሬ ከቤት አትወጭም!
እንደዚህ ሆኖ ይወጣል? ሰው ሞቱን ነው ወይ የሚፈልገው?" ሲሉ ከልክለዋት ነበር።
በጊዜው እርሷም ፍርሃትና ጭንቀት ገብቷት እንደነበር አልደበቀችም "ከበረራ
በፊት ውይይት ስናደርግ ሕይወታቸው ያለፉት አስተናጋጆች ትዝ ይሉን ነበር፤ ድባቡ ያስጠላ ነበር፤ ከባድ ነበር ...እንቅልፍ ሁሉ
ነስቶኝ ነበር" ትላለች።
"አደጋው የደረሰው አውሮፕላኑ ከተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ስለነበር የተከሰከሰው፤ እኛም አውሮፕላኑ ገና ሲነሳ ሁሉም እያለቀሰ ነበር፤ አገልግሎት
መስጠት ተስኖን ነበር" ስትል ታስታውሰዋለች።
ከበፊት ጀምሮ ከቤት ስወጣ "ለእግዚያብሔር አደራ ሰጥቼ ነበር የምወጣው፤
አሁንም ይህንኑ ማድረግ የዘወትር ተግባሬ ነው" ትላለች።
የሕግ ምሩቅ የሆነችው ይህች አስተናጋጅ ቤተሰቦቿ በአደጋ ምክንያት በስጋት መኖራቸው
አልቀረም ታዲያ "አባቴ በተመረቅኩበት ትምህርት እንድሠራ ማስታወቂያዎችን እያየ ሞክሪ!... እስከመቼ ተሳቀን እንኖራለን"
ሲሉ ይወተውቷት ነበር። እርሷ ግን ሥራዋን አብዝታ ስለምትወደው የእነርሱን ውትዎታ ከቁብም አልቆጠረችው።