ኤል ጂ ኤሌክትሮኒክስ ተብሎ በሚጠራ ድርጅት የማርኬቲንግ ኃላፊ የሆነው ሂራም ማሻሪያ የመጀመሪያውን ፍንዳታ እንደሰማ ለማምለጥ ሙከራ አድርጎ እንደነበር ለሬውተርስ የዜና አገልግሎት ተናግሯል።
“የእሳት ማጥፊያውን ይዤ ወደታች ልንወርድ ስንል፤ ከአሸባሪዎቹ መካከል ሁለቱ ወደ አሳንሰሩ ሲተኩሱ ስናይ ተመልሰን ከጠረጴዛችን ስር ተደበቅን” ብሏል።
አክሎም "ደረጃውንም እየወጡ የአሳንሰሩ በሮችና ወደ ደረጃዎቹ የሚወስዱት በሮች ላይ ሁለት ጊዜ ተከሱዋል።። ከተኳሹ አንዱ የቢሮያችን በር ላይ አንድ ጊዜ ተኩሶ ብቅ ብሎ ትቶን ሄደ”
ማሻሪያ እንደገለፀው በቢሮው ተደብቆ የቀረ ሲሆን ወደ ጣሪያው የሮጠው የሥራ ባልደረባው ግን ተገድሏል።
‘ከመውጣታችን በፊት የስልክ መልዕክት ደርሶን ነበር’
ከፓሪስ ለስራ የመጣው ማማዱ ዲያ በሽብር ጥቃቱ መሃል እራሱን አገኘው።
በሆቴሉ አርፈው ከነበሩ ካናዳዊና ቻይናዊ እንግዶችና ከሆቴል አስተናጋጅ ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ ተደብቀው ነበር።
"ፖሊሶች የተደበቅንበትን ክፍል እንደሚያውቁና ከአንድ ሰዓት ተኩል በኋላ መጥተው እንደሚያድኑን አጭር የስልክ መልእክት ደርሶን ነበር" ብሏል።
ፖሊሶቹ መጥተው ሲያስወጧቸውም ተኳሾቹ እንደሰለጠኑ አልሞ ተኳሾች ሲተኩሱ እንደነበር ተናግሯል።