"የአሜሪካ ጥቃት ኢራንን የማንበርከክ እንጂ ከኒውክሌር ጋር ምንም ግንኙነት የለውም"- አያቶላህ ኻሜኒ

አሜሪካ በኢራን የፈጸመችው ጥቃት "ኢራንን እጅ የማሰጠት" እንጂ በጭራሽ ከኒውክሌር ማበልጸግ ጋር ፍጹም ግንኙነት እንደሌለው የአገሪቱ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ኻሜኒ ተናገሩ።ከሳምንት በኋላ የታዩት ጠቅላይ መሪው “ሁልጊዜም ቢሆን አንድ ነገር ብቻ ነው ፍላጎታቸው፤ ኢራን እጇን እንድትሰጥ” ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

  • እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የአገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ሳኢድ ኢዛዲ መገደላቸውን የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ማረጋገጡን የአገሪቱ ሚዲያ ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።
  • የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ኢራን ከአሜሪካ ጥቃት በፊት የበለጸገ የዩራኒየም ክምችቷን ከፎርዶ የኒውክሌር ጣቢያ አዛውራለች የሚለውን ሪፖርት አስተባበሉ።
  • በኳታር የአሜሪካ የጦር ሰፈርን ለመከላከል የቀሩት 44 ወታደሮች ብቻ እንደነበሩ አሜሪካ ገለጸች
  • አሜሪካ 'ኦፕሬሽን ሚድናይት ሐመር' በሚል ስያሜ በኢራን ላይ የፈጸመችው ጥቃት ለ15 ዓመታት የታቀደበት እንደሆነ የአገሪቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ዳን ኬይን ገለጹ።
  • በኢራን ላይ የተፈጸመው "የተሳካ ታሪካዊ ጥቃት ነበር" ሲሉ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ገለጹ
  • አሜሪካ በኢራን የፈጸመችው ጥቃት ኢራንን እጅ የማሰጠት እንጂ በጭራሽ ከኒውክሌር ማበልጸግ ጋር ፍጹም ግንኙነት እንደሌለው የአገሪቱ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ኻሜኒ ተናገሩ
  • ትራምፕ፤ የአሜሪካ ጥቃት የኢራን ኒውክሌር ይዞታዎችን አላወደመም የሚለውን የደህንነት ግምገማ ውድቅ አደረጉ
  • የአሜሪካ ጥቃት የኢራን ኒውክሌር ይዞታዎችን እንዳላወደመ የደህንነት ግምገማ አሳየ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኢራን ከፍተኛ የጦር አዛዧ መገደላቸውን አረጋገጠች

    ሳኢድ አዛዲ እና ሌሎች አመራሮች

    የፎቶው ባለመብት, Iran government

    እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት የአገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ሳኢድ ኢዛዲ መገደላቸውን የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ማረጋገጡን የአገሪቱ ሚዲያ ታስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ኢዛዲ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ቅርንጫፍ የሆነው 'ቁድስ ፎርስ' ከፍተኛ አዛዥ ነበሩ።

    ይህ ቅርንጫፍ በቀጣናው ያሉ የኢራን አጋር ታጣቂዎችን ድጋፍ ማድረግን ጨምሮ በውጭ አገራት ያሉ እንቅስቃሴዎችን በበላይነት የሚያይ ነው።

    አዛዡ ከሐማስ እና ከሌሎች የፍልስጤም ታጣቂ ቡድኖች ጋር የማስተባበር ኃላፊነት የሳቸው ነበር።

    አብዮታዊ ዘቡ አዛዡ መቼ እንደተገደሉ ያለው ነገር ባይኖርም የእስራኤል መከላከያ ሰኔ 14 / 2017 ዓ.ም መገደላቸውን አስታውቋል።

    ዩናይትድ ኪንግደም "በመካከለኛው ምስራቅ ሰላም እና ደህንነት ስጋቶችን በመፍጠር" እንዲሁም "በዩኬ መሬት ላይ ግለሰቦችን ለመግደል በማሴር" በሚል በአዛዡ ላይ በአውሮፓውያኑ 2023 ማዕቀብ ጥላባቸው ነበር።

    አሜሪካ በአውሮፓውያኑ 2019 ለሐማስ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ሰጥተዋል በሚል በጦር አዛዡ ላይ ማዕቀብ ጥላባቸዋለች።

  2. ትራምፕ ኢራን ከጥቃቱ በፊት የዩራኒየም ክምችቷን አንቀሳቅሳለች የሚለውን ሪፖርት አስተባበሉ

    ፎርዶው

    የፎቶው ባለመብት, Maxar Technologies

    የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ኢራን ከአሜሪካ ጥቃት በፊት የበለጸገ የዩራኒየም ክምችቷን ከፎርዶ የኒውክሌር ጣቢያ አዛውራለች የሚለውን ሪፖርት አስተባበሉ።

    ትራምፕ “ከተቋሙ ምንም ነገር አልወጣም” ሲሉ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

    አክለውም “በጣም ረዥም ጊዜ የሚወስድ ነው፣ በጣም አደገኛ እንዲሁም በጣም ከባድ እና ለማንቀሳቀስም አስቸጋሪ ነው” ብለዋል።

    ይልቁንም በይዞታው ላይ የታዩት “ተሽከርካሪዎች እና ትናንሽ የጭነት መኪናዎች” የአየር ማስተላለፊያዎቹን ቋሚዎች በግንባታ ለመሸፈን ሲሞክሩ የነበሩ ሰራተኞች ናቸው ብለዋል።

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት ይህንኑ ሪፖርት ውድቅ አድርገውታል።

  3. በኳታር የአሜሪካ የጦር ሰፈርን ለመከላከል የቀሩት 44 ወታደሮች ብቻ እንደነበሩ አሜሪካ ገለጸች

    አል ኡደይድ የጦር ሰፈር

    የፎቶው ባለመብት, USAF

    ኢራን በኳታር በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ጥቃት ከመፈጸሟ በፊት አብዛኛዎቹ ወታደሮች እንዲወጡ መደረጉንና የቀሩት 44 ወታደሮች ብቻ እንደነበሩ የአገሪቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ዳን ኬይን በዛሬው ዕለት ገልጸዋል።

    “ሰኞ ማለዳ ላይ ኢራን በቀጣናው በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃቶች ለመፈጸም እንዳሰበች ማስጠንቀቂያ ይደርሰን ጀመር” ብለዋል።

    በፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ መሰረት “በጥቂት ኃይል ለመከላከል” ተወስኖ በርካታ ወታደሮች ከጦር ሰፈሩ እንዲወጡ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

    የጦር ሰፈሩን የመጠበቅ ኃላፊነት የተጣለባቸው “44 ወታደሮች እንደቀሩ” ተናግረዋል።

    በዕድሜ ትልቁ የነበረው ወታደር 28 እንደነበር እና ትንሹ ደግሞ በውትድርና አገልግሎት ለሁለት ዓመት የቆየ የ21 ዓመት ልጅ ነበር ብለዋል።

    አል ኡደይድ የጦር ሰፈርን ለመከላከል ኳታር እንዳገዘች ገልጸው፤ የአየር ተከላካዮቹ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለመወሰን ሰኮንዶች ብቻ ነበራቸው ብለዋል።

  4. አሜሪካ በኢራን ላይ የፈጸመችው ጥቃት የ15 ዓመታት ዕቅድ “ፍጻሜ” ነው

    የአገሪቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ዳን ኬይን

    የፎቶው ባለመብት, US Department of Defense

    አሜሪካ ‘ኦፐሬሽን ሚድናይት ሐመር’ በሚል ስያሜ በኢራን ላይ የፈጸመችው ጥቃት ለ15 ዓመታት የታቀደበት እንደሆነ የአገሪቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ዳን ኬይን ገለጹ።

    ጄኔራሉ አገራቸው የተጠቀመችባቸው ቦምቦች ከመሬት በታች በጥልቀት ለተገነባው የፎርዶ ኒውክሌር ጣቢያን ለማጥቃት “የተነደፉ፣ የተቃዱ” በመጨረሻም ጥቃት የተፈጸመባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

    አሜሪካ ‘በንከር በስተር የተሰኘውን ቦምቧን የሰራችው የፎርዶ የኒውክሌር ማብላያን ለማጥቃት እንደሆነም አስረድተዋል።

    የይዞታው ሁለት የአየር መተላለፊያ ቋሚዎች ተመትተዋል ያሉት ኤታማዦር ሹሙ፤ ኢራናውያን ጥቃቱን ለመከላከል በግንባታዎች ለመሸፈን ቢሞከሩም አልታደገውም ሲሉ አክለዋል።

    ሁለቱ የአየር መተላላፊያ ቋሚዎች በመጀመሪያ ጥቃት ሲመቱ ከላይ ሸፍኗቸው የነበረው ግንባታ በመውደሙ በዚህም አምስት ተጨማሪ ቦምቦች ከመሬት በታች ውስጥ ገብተው “በይዞታው ላይ ፈንድተዋል” ብለዋል።

    አሜሪካ ኢራን ከመሬት በታች ጥልቀት ያለው የኒውክሌር ይዞታ እየገነባች ስለመሆኗ መረጃ የደረሳት ከአመታት በፊት እንደነበር አስረድተዋlእ።

    የአሜሪካ መከላከያ ስጋት ቅነሳ ኤጀንሲ መኮንን ፎርዶን ለአስራ አምስት ዓመት ሲያጠናው እንደነበር ገልጸዋል።

  5. በኢራን ላይ የተፈጸመው “የተሳካ ታሪካዊ ጥቃት ነበር” የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት አገራቸው የፈጸመችው ጥቃት የኢራንን የኒውክሌር አቅምን “ሙሉ በሙሉ ያወደመ ነው” ሲሉ ተናገሩ።

    ሚኒስትሩ፤ ትራምፕ “በታሪክ ውስጥ እጅግ ውስብስብ እና ሚስጥራዊ የሆነውን ወታደራዊ ዘመቻ መርተው፤ አስደናቂ ስኬትን ተጎናጽፈዋል ብለዋል።

    የመከላከያ ሚኒስትሩ ይህንን ንግግራቸውን ለማጠናቀር ዋቢ ያደረጉት አንደኛው የእስራኤል አቶሚክ ኤጀንሲ ያወጣውን መግለጫ ነው።

    ጥቃቱ “የኢራንን የማበልጸጊያ ተቋማት ከአገልግሎት ውጭ አድርጓቸዋል” ሲል ኤጀንሲው ገልጾ ነበር።

    በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ኃላፊ በኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ “ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል” ማለታቸውን ሚኒስትሩ ማጣቀሻ አድርገውታል።

    ከዚህም በተጨማሪ ሲአይኤም በተመሳሳይ መልኩ የደረሰበትን ማጠቃለያ ጠቅሰው “ይዞታዎቹ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል” ብለዋል።

    አሜሪካ በኢራን ላይ የፈጸመችው ጥቃት የኒውክሌር ማብላያ ይዞታዎችን እንዳላወደመ ሾልኮ የወጣ የአሜሪካ መከላከያ ማዕከል (ፔንታጎን) የደህንነት ግምገማ አሳይቷል። ቅድመ ግምገማው ጥቃቱ የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ምናልባትም በወራት ወደኋላ ሊመልሰው እንደሚችል ነው ያሳየው።

    ይህንን ሾልኮ የወጣ መረጃ የጠቀሱት ሚኒስትሩ “ቅድመ ግምገማ” ነው ሲሉ አጣጥለው ጥቃቱ ብዙም ስኬታማ እንዳልነበር የማሳየት "አጀንዳ" በሚዲያዎች ተይዞ ነበር ሲሉ አጣጥለዋል። “ኃላፊነት የጎደለው” ሲሉ ሚዲያዎቹንም ተችለተዋል።

    “ለምን አንደሰትበትም? ይህ ታሪካዊ ጥቃት ነው እናም እንደ አሜሪካውያን ልንደሰትበት ይገባል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

  6. “በእስራኤል እና አሜሪካ ላይ ድል ተቀዳጅተናል” አያቶላህ ኻሜኒ

    አያቶላህ ኻሜኒ እና ፕሬዚዳንት ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ኻሜኒ በእስራኤል እና አሜሪካ ላይ ድል ተቀዳጅተናል አሉ።

    ኻሜኒ አሜሪካ በቀጥታ ጦርነት ውስጥ የገባችው “የጽዮናውያን አገዛዝ ሙሉ በሙሉ እንደሚወድም ስለተሰማት ነው፤ ነገር ግን አሜሪካ ምንም አላተረፈችም" ሲሉ ነው የተናገሩት።

    ጠቅላይ መሪው አገራቸው በድል አድራጊነት ወጥታለች ያሉ ሲሆን፤ ለአሜሪካ ጥቃት "አጸፋውን ምላሽ እንደሰጠችም ነው የገለጹት።

    አክለውም “በጽዮናውያን አገዛዝ ላይ ስለተጎናጸፍነው ድል እንኳን ደስ አላችሁ” ሲሉ ለህዝባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    ኻሜኒ አሜሪካ በአገራቸው ጥቃት ከፈጸመች እንዲሁም ከእስራኤል ጋር የነበረው ግጭት ከቆመ በኋላ ባስተላለፉት የመጀመሪያ መልዕክት ነው ይህንን ያሉት።

    የኢራን ህዝብ አንድነቱን በማሳየት “ህዝባችን አንድ ድምጽ ነው ያለው” የሚል መልዕክት አስተላልፏል" ሲሉም ለህዝቡ ምስጋና አቅርበዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራንን “እጅ እንድትሰጥ” መጠየቃቸውን የጠቀሱት ኻሜኒ አስተያየታቸው “ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት አንደበት በጣም ትልቅ ነው” በማለት ተችተዋል።

    ኻሜኒ አክለውም “እንደ ኢራን ላለ ታላቅ አገር እና ህዝብ እጅ ስጡ ማለት ስድብ ነው፤ እጅ መስጠት የሚለው ቃል በመዝገበቃላችን ውስጥ የለም" ብለዋል።

    ትራምፕ በዚህ አጋጣሚ አንድ እውነት እንደገለጡ የጠቀሱት ኻሜኒ አሜሪካውያን የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክን መቃወም ገና ከጅምሩ ሲቃወሙ መቆየታቸውን ነው ሲሉም አክለዋል።

  7. “አሜሪካ በኢራን በፈጸመችው ጥቃት ጠቃሚ ነገር ሳታሳካ አጋንናዋለች”- ኻሜኒ

    ኻሜኒ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አሜሪካ በኢራን ኒውክሌር ይዞታዎች ላይ “ምንም ጠቃሚ ነገር ማሳካት አልቻለችም” ሲሉ አያቶላህ ኻሜኒ ገለጹ።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተፈጸመው ጥቃት ምን እንዳደረሰ “ባልተለመደ መልኩ አጋንነው”አቅርበውታል ሲሉ ኻሜኒ ተችተዋል።

    ይህንን ማድረግ ያስፈለጋቸው ምክንያት ግልጽ ነበር የሚሉት ኻሜኒ "አሜሪካ ያጋነነችበት ምክንያት እውነቱን ለማጣመም እንደሆነ የሰማቸው በሙሉ ይረዳል” ብለዋል።

    ኢራን በቀጣናው ከሚገኙ የአሜሪካ ቁልፍ የጦር ሰፈሯቿ በአንዱ ላይ ጥቃት መፈጸሟን አስታውሰው ይህንንም ለማሳነስ ሞክረዋል ሲሉ ገልጸዋል።

  8. “የአሜሪካ ጥቃት ኢራንን የማንበርከክ እንጂ ከኒውክሌር ጋር የተገናኘ አይደለም”- አያቶላህ ኻሜኒ

    አያቶላህ ኻሜኒ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አሜሪካ በኢራን የፈጸመችው ጥቃት ኢራንን እጅ የማሰጠት እንጂ በጭራሽ ከኒውክሌር ማበልጸግ ጋር ፍጹም ግንኙነት እንደሌለው የአገሪቱ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ኻሜኒ ተናገሩ።

    “አንድ ቀን ስለ ሰብዓዊ መብት፣ ሌላ ጊዜ ስለ ሴቶች መብት፣ ከዚያ ደግሞ ኒውክሌር በመቀጠል ደግሞ ሚሳኤሎች ያነሳሉ” ሲሉ ኻሜኒ ተችተዋል።

    ከሳምንት በኋላ የታዩት ጠቅላይ መሪው መሰረታዊው ነገር “ሁልጊዜም ቢሆን አንድ ነገር ብቻ ነው ፍላጎታቸው፤ ኢራን እጇን እንድትሰጥ” ብለዋል።

  9. አሜሪካ ኢራን ላይ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ኤፍቢአይ በፀረ ሽብርተኝነት ላይ ትኩረት አጠናክሯል

    የፖሊስ ልብስ ለብሰው ጀርባቸውን የሰጡ ሁለት ሰዎች እና አንድ ሰው

    የፎቶው ባለመብት, DEPARTMENT OF HOMELAND SECURITY

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ባለሥልጣናት ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን 11 ኢራናውያንን በቁጥጥር ስር አውለዋል

    አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ከፈፀመች በኋላ በመላው አሜሪካ የሚገኙ ባለሥልጣናት በአሜሪካ ውስጥ ሊሰነዘር ለሚችል ጥቃት በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸው ተገለፀ።

    ፕሬዚደንት ትራምፕ ሰነድ አልባ ዜጎችን ከአገር ለማስወጣት በሚወስዱት እርምጃ ላይ ይሰሩ የነበሩ አንዳንድ የኤፍቢአይ ባልደረቦች በፀረ ሽብርተኝነት ላይ እንዲያተኩሩ መደረጉን የቢቢሲው የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።

    እሁድ ዕለት ቢሮው በሽብር ስጋት ላይ ትኩረታቸውን እንዲያጠናክሩ የሚገልጽ ማስታወሻ ለመስክ ቢሮዎቹ አሰራጭቷል።

    ኤፍቢአይ ምንም ዓይነት የትኩረት ለውጥ ስለማድረጉ ማረጋገጫ አልሰጠም።

    ኤጀንሲው በሰጠው መግለጫ "ኤፍቢአይ በተለዩ የአሠራር ማስተካከያዎች ወይም የሠራተኞች ውሳኔ ላይ አስተያየት አይሰጥም" ብሏል።

    "ይኹን እንዲ በብሔራዊ ደህንነታችን ላይ ለሚደርሱ በጣም አሳሳቢ ስጋቶች ምላሽ ለመስጠት እና የአሜሪካን ሕዝብ ደህንነት ለማረጋገጥ አቅማችንን በተከታታይ እንፈትሻለን እንዲሁም እናስተካክላለን።"

    ምንም የተለየ ስጋት የለም፣ ነገር ግን በቅርብ ቀናት ውስጥ የአሜሪካ ባለስልጣናት በሕገ ወጥ መንገድ በአሜሪካ ውስጥ የነበሩ 11 ኢራናውያንን በቁጥጥር ስር አውለዋል።

    በርካቶች ከኢራን ወታደራዊ ወይም ከሚሊሻ ተወካዮች ጋር ግንኙነት ነበራቸው ተብሏል።

  10. ኢራን ከፍተኛ የጦር አዛዥ መሞታቸውን አረጋገጠች

    ሜጀር ጄኔራል አሊ ሻድማኒ

    የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/SHUTTERSTOCK

    የምስሉ መግለጫ, ሜጀር ጄኔራል አሊ ሻድማኒ

    ኢራን የኢስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ጓድ የካታም አል አንቢያ ማዕከላዊ ዋና መስሪያ ቤት አዛዥ አሊ ሻድማኒ መሞታቸውን አስታወቀች።

    የኢራን መንግሥት ሚዲያ በዘገባው ላይ የዋናው መሥሪያ ቤቱ የሰጠውን መግለጫ ጠቅሷል።

    ሻድማኒ ባለፈው ሳምንት እስራኤል ባደረገችው ድብደባ በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን ተገልጿል።

    ሻድማኒ የኢራን ጥምር ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያስተባብረው የአብዮታዊ ዘቡ ካህታም አል አንቢያ የተሰኘው ማዕከላዊ ዋና መስሪያ ቤት ኃላፊ ሆነው በተሾሙ በጥቂት ቀናት ውስጥ ነበር በእስራኤል የአየር ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው።

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ሰኔ17 ባወጣው መግለጫ ሻድማኒ የተገኘ “ትክክለኛ መረጃን ተከትሎ” መገደላቸውን አስታውቆ ነበር።

    ሻድማኒ የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኔይ ረዳት ሲሆኑ የአገሪቱ “የጦር ጊዜ ዋና አዛዥ” በመባል ይታወቁ ነበር።

    ሻድማኒ የካታም አል-አንቢያ አዛዥ ሆነው የተሾሙት በእስራኤል የአየር ጥቃት የቀድሞው አዛዥ ጎላማሊ ራሺድ መገደላቸውን ተከትሎ ነበር።

  11. የኒውክሌር ተቋማት እና ሳይንቲስቶች "ጥበቃ እና ከለላ" ሊደረግላቸው ይገባል- የኢራን ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ አካል ጋር ያለውን ትብብር ለማቆም ያቀደው በኢራን ላይ ለሚሰነዘረው "ሕገ ወጥ ጥቃት" ምላሽ ነው ሲል መናገሩን የኢራን ስቱደንትስ ኒውስ ኤጀንሲ ዘገበ።

    "የእኛ የኒውክሌር ተቋማት እና ሳይንቲስቶች ጥበቃ እና ከለላ ሊደረግላቸው ይገባል" ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ መሀመድ ባገር ጋሊባፍ የአገሪቱ የኒውክሌር ባለስልጣናት "የኒውክሌር ተቋማቱ ደህንነት እስኪረጋገጥ ድረስ ከዓለም አቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር ያለውን ትብብር ያቆማሉ" ብለዋል።

    ይህንን ውሳኔ ለማሳለፍ ተጨማሪ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ድምጽ ሊሰጡበት ይገባል።

  12. ትራምፕ አሜሪካ እና ኢራን በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚገናኙ ተናገሩ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ትራምፕ ከኢራን ጋር በቀጣይ ስለሚኖረው እና የዩናይትድ ስቴትስ ጥቃት ከመፈፀሟ በፊት የኒውክሌር ቁሳቁሶችን አውጥታ እንደሆን ተጠይቀዋል።

    ትራምፕ ሲመልሱ በተቃራኒው ነው የሆነው፤ኢራን የኒውክሌር እቃዎቿን ለማንቀሳቀስ ጊዜ አልነበራትም ብለዋል።

    "በጣም ከባድ እና ለመንቀሳቀስ በጣም አስቸጋሪ ነው" ካሉ በኋላ፣ኢራን የኒውክሌር አቅም "ነበራት" ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮተጨማሪ ሃሳብ እንዳላቸው ተጠይቀው፣ ትራምፕ ሰላም የሚፈልጉትን ለማነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውን አሳይተዋል ብለዋል።

    ሩቢዮ አክለውም ድርድሩ እንደገና እንዲጀመር ኢራን ለመሳተፍ ባላት ፈቃደኝነት ላይ ይወሰናል ብለዋል።

    ትራምፕ በሚቀጥለው ሳምንት ከኢራን ጋር "እንነጋገራለን" ሲሉ ስምምነት ሊፈራረሙ እንደሚችሉም ተናግረዋል።

    "እንደዚያ አስፈላጊ አይመስለኝም።ጦርነት ውስጥ ነበሩ። ተዋግተዋል፤ እና አሁን ወደ ዓለም ይመለሳሉ። ስምምነት ቢኖረኝም ባይኖረኝም ግድ የለኝም" ብለዋል።

    "ከእነሱ ጋር እንገናኛለን።"

  13. “አብቅቷል፣ ዳግመኛ ወደ መታኮስ የሚመለሱ አይመስለንም”- ትራምፕ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ዶናልድ ትራምፕ በኔዘርላንድስ እየተካሄደ በሚገኘው ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር በኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ የተካሄደውን “ግዙፍና ዒላማውን የጠበቀ ጥቃት” በማወደስ ጀምረዋል።

    "በምድር ላይ ሌላ መከላከያ ሊሰራው አይችልም ነበር።እናም ይህ አስደናቂ የአሜሪካ ጥንካሬ አሁን ለሰላም መንገድ ጠርጓል" ብለዋል።

    ትራምፕ አክለውም “አብቅቷል፣ ዳግመኛ ወደ መታኮስ የሚመለሱ አይመስለንም” ብለዋል።

    ፕሬዚዳንቱ በመቀጠል ኢራንን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳይኖራት ማድረግ እንዲሁም "የአሜሪካን የመከላከል ተዓማኒነት በድጋሚ አረጋግጠናል" ብለዋል።

    ዶናልድ ትራምፕ ኢራን በኳታር የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ከመፈፀሟ በፊት "ማስጠንቀቂያ" መስጠቷን ተናግረዋል።

    ትራምፕ ኢራንን ጠቅሰው "አንድ ሰዓት በቂ ነው?" ብለው መጠየቃቸውን እና ዋሽንግተን “ጥሩ ነው” የሚል ምላሽ መስጠቷን ተናግረዋል።

    የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት አሜሪካ ለተኮሰቻቸው 14 ሚሳዔሎች ቴህራንም 14 መተኮሷን ተናግረዋል።

    ኢራን ሰኞ ዕለት በኳታር በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሠፈር ላይ ሚሳኤሎችን ተኩሳለች።

    ይህም አሜሪካ በሳምንቱ መጨረሻ በኒውክሌር ተቋማቷ ላይ ላደረሰችው ድብደባ የበቀል እርምጃ በሚል ነው።

    ኢራን ስላስወነጨፈቻቸው ሚሳኤሎች ብዛት የተለያዩ መረጃዎች ወጥተዋል።

    ኢራን ስድስት ሚሳዔሎችን ማስወንጨፏን ስትናገር፣ አሜሪካ 14 ኳታር ደግሞ 19 ብለዋል።

    ሁሉም ሚሳዔሎች ግን በአየር ላይ ሳሉ እንዲከሽፉ መደረጉን የኳታር መንግሥት በወቅቱ ገልጿል።

  14. የእስራኤል የኒውክሌር ባለሥልጣን ፎርዶ የኒውክሌር ተቋም ከድብደባው በኋላ “ከሥራ ውጪ ሆኗል” አለ

    የፎርዶ የኒውክሌር ተቋምን የሚያሳይ የሳተላይት ምስል

    የፎቶው ባለመብት, MAXAR

    የእስራኤል መንግሥት የኒውክሌር ባለሥልጣን አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የፈጸሙት ጥቃት መሬት ውስጥ የሚገኘውን የኢራን የኒውክሌር ማበልጸጊያ፣ ፎርዶን "ከሥራ ውጪ አድርጎታል" ብሏል።

    የእስራኤል የአቶሚክ ኢነርጂ ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ የአየር ድብደባውን “አውዳሚ” ያለ ሲሆን “የተቋማቱን ወሳኝ መሠረተ ልማት አውድሟል” ብሏል።

    “አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ ያደረሰችው ጥቃት፣ እስራኤል በሌሎች የኢራን ወታደራዊ የኒውክሌር መርሃ ግብሮች ላይ ያደረሰችው ድብደባ የኢራንን የኒውክሌር ጦር መሣሪያን የማልማት አቅም በብዙ ዓመታት ወደ ኋላ እንደመለሰው ገምግመናል።”

    የእስራኤል የአቶሚክ ኢነርጂ ባለሥልጣን አክሎም "ኢራን የኒውክሌር ማምረቻዎችን የማታገኝ ከሆነ ስኬቱ ላልተወሰነ ጊዜ ሊቀጥል ይችላል።"

    መግለጫውን በመጀመሪያ በዋይት ሐውስ በኩል ለጋዜጠኞች የተሰራጨ ሲሆን በኋላም በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በኩል ይፋ ሆኗል።

    ቀደም ሲል ከአሜሪካ የደህንነት መስርያ ቤት ሾልኮ የወጣ መረጃ አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር መሥሪያ ቤቶች ላይ ያደረሰችው ጥቃት የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር አላወደመም፤ ምናልባትም “በጥቂት ወራት ብቻ ወደ ኋላ መልሷት ይሆናል” ማለቱ ይታወሳል።

  15. የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር የተኩስ አቁሙ መቀጠል አለበት አሉ

    የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር

    የፎቶው ባለመብት, PA Media

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር በኔዘርላንድስ እየተካሄደ በሚገኘው የኔቶ ጉባኤ ላይ ንግግር አድርገዋል።

    ስታርመር "ይህን እድል ተጠቅሞ አካባቢውን ለማረጋጋት ጊዜው አሁን ነው" ያሉ ሲሆን በእስራኤል እና በኢራን መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መቀጠል አለበት ብለዋል።

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር ወደ ድርድር ጠረጴዛ መመለስ አለባት ሲሉም አክለዋል።

    "በዚህ መልኩ ነው የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር በሙሉ ማብቃቱን፣መፈተሹን እና ሊቀለበስ በማይችል መልኩ ፍፃሜውን ማግኘቱን የምናረጋግጠው" ብለዋል።

    "ይህንን ጥረት ለመደገፍ እያንዳንዱን ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እንጠቀማለን።"

    የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመቀጠል ከቀጠናው መሪዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዳላቸው ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ስታርመር “ኢራን በግዴለሽነት ጥቃት ከሰነዘረች በኋላ” አጋርነታቸውን ለመግለጽ ትናንት የኳታርን አሚር ማነጋገራቸውን ተናግረዋል።

  16. በኢራን የአውሮፕላን በረራዎች እስከ ነገ ምሽት ድረስ ተሰርዘው ይቆያሉ ተባለ

    በኢራን አጠቃላይ የአገር ውስጥ እና የውጭ በረራዎች እስከ ነገ ምሽቱ 2 ሰዓት ድረስ ተሰርዘው እንደሚቆዩ ሜህር የዜና ወኪል ዘግቧል።

    በኢራን መንግሥት ከፊል ባለቤትነት የሚተዳደረው የዜና ተቋሙ ለዘገባው የኢራን የመንገድ እና የከተማ ልማት ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማጂድ አካቫን ጠቅሷል።

    ዘገባው አክሃቫን ተጨማሪ መግለጫ እስኪሰጥ ድረስ የበረራ ትኬቶች በአየር መንገዶችም ሆነ በወኪሎቻቸው አይሸጡም ብሏል።

  17. ክሬምሊን በኢራን ላይ የተፈጸመው ጥቃት ከተባበሩት መንግሥታት ተቆጣጣሪ ጋር ያላትን ትብብር እንድታቋርጥ እንዳስገደዳት ገለፀች

    የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ የተፈጸመው ጥቃት አገሪቱ የተባበሩት መንግሥታት የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ከሆነው ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) ጋር ያላትን ትብብር እንድታቆም አስገድዷታል ብለዋል።

    "ይህ ውሳኔ በኢራን ላይ ያለ ምንም ትንኮሳ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የኒውክሌር ተቋማቷ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት ቀጥተኛ ውጤት ነው" ሲሉ በዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።

    ፔስኮቭ "በዚህ ሁኔታ የኤጀንሲው መልካም ስም በጣም ተጎድቷል። ስለዚህ ይህ ሁኔታ ስጋትን ያጭራል" ብለዋል።

    በኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ ስለደረሰው ጉዳት የሚወጡ እርስ በርስ የሚጋጩ ዘገባዎችን በተመለከተ ፔስኮቭ ሲናገሩ “አንድም ሰው እስካሁን ተጨባጭ መረጃ ያለው አይመስለኝም” በማለት የጉዳቱን መጠን ለመናገር በጣም ገና ነው ብለዋል።

    በሩሲያ የዜና አውታሮች ላይ በሰጡት አስተያየት ጥቃቱን የፈጸሙትን አገሮች በስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።

    ሞስኮ ኢራንን እንደ አጋር የምታይ ሲሆን፣ በቅርቡ የተፈፀመውን ጥቃት “ያለምንም ትንኮሳ” የተፈጸመ በማለት አውግዛለች።

    በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ፔስኮቭ በሞስኮ እና በዋሽንግተን መካከል ባለው የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተፅእኖ አሳንሰው አቅርበዋል።

  18. በኢራን የኢንተርኔት አገልግሎት ዳግም መጀመሩ ተገለፀ

    የኢራን የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር በአገሪቱ ውስጥ ያለው የኢንተርኔት አገልግሎት ወደ “ቀድሞ ሁኔታው” መመለሱን ገለፁ።

    የእስራኤል ጥቃት እየተጠናከረ መምጣቱን ተከትሎ የኢራን መንግሥት የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ አድርጎ የነበረ ሲሆን የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር አድርጓል።

    ሳታርሃሺሚ ኢራን "ዳግመኛ ተመሳሳይ ነገር አይገጥማትም" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ለጥፈዋል።

    እአአ ሰኔ 17 የኢራን መንግሥት "የሳይበር ጥቃቶችን ለመዋጋት" በሚል የኢንተርኔት ፍጥነት እንዲቀንስ አድርጎ ነበር።

    ይሁን እንጂ በአጠቃላይ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ ተሰምቷል።

    እንደ ኤክስ ባሉ ዋና ዋና የማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተጣለው እገዳ አሁንም እንዳለ ነው።

    በኢራን የሚኖሩ ዜጎች እነዚህን የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ለመክፈት ቪፒኤን እና ሌሎች ዘዴዎችን ይጠቀማሉ።

    ምንም እንኳ እገዳ ቢጣልባቸውም እንደ የኢራን ጠቅላይ መሪ ያሉ በርካታ የኢራን ባለስልጣናት የኤክስ ገጾች አሏቸው።

  19. አሜሪካ ጥቃት ስለፈፀመችባቸው የኢራን የኒውክሌር ተቋማት ማን ምን አለ?

    የኢስፍሃን የኒውክሌር ተቋም

    የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

    የምስሉ መግለጫ, የኢስፍሃን የኒውክሌር ተቋም በአሜሪካ ድብደባ ከተፈጸመባቸው መካከል አንዱ ነው

    በሳምንቱ መጨረሻ ላይ አሜሪካ በኢራን ሦስት የኒውክሌር ተቋማት ላይ ጥቃት ፈጽማለች። ስለ ጥቃቱ ማን ምን አለ?

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ስለተፈጸመው የአየር ጥቃት ሲናገሩ የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር “በአስርታት” ወደ ኋላ መልሰነዋል ብለዋል።

    ይህንን ያሉት ሾልኮ የወጣ የደህንነት ሰነድ የአሜሪካ የአየር ጥቃት የኢራንን የኒውክሌር ተቋማት “በተወሰኑ ወራት” ወደ ኋላ ከማዘግየት በስተቀር አላወደማቸውም ካለ በኋላ ነው።

    የአሜሪካ መከላከያ ሚንስትር ፔት ሄግዝ ዘመቻውን “እንከን የለሽ” ካሉ በኋላ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት ሾልኮ የወጣውን መረጃ “ፖለቲካዊ ዓላማ አለው” ብለዋል።

    የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ምክትል የፖለቲካ ዳይሬክተር ሀሰን አቤዲኒ በአሜሪካ ዒላማ የተደረጉትን ሦስቱ ተቋማትን "ከተወሰነ ጊዜ በፊት" ለቅቀው መውጣታቸውን ተናግረዋል። ኢራን "ቁሳቁሶቹ ቀደም ብለው ስለወጡ ምንም ጉዳት አልደረሰባትም" ሲሉ አስተባብለዋል።

    እስራኤልም የራሷን ጥቃት በኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ የፈጸመች ሲሆን፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እንዳሉት አገሪቱ የኢራንን የኒውክሌር ፍላጎት በመገደብ እና የሚሳኤል ትጥቆቿን በማውደም ውጤታማ ናት።

    የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ ኢራን ለኒውክሌር መርሃ ግብሯ የኢንዱስትሪ አቅሟን እና ቴክኒካል እውቀቷን እንደያዘች መካድ አይቻልም ብለዋል።

  20. ትራምፕ ጥቃቱ የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን በአስርታት ወደኋላ የመለሰ ነው አሉ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው የፈጸመችው ጥቃት የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን በአስርት ዓመታት ወደ ኋላ የመለሰ ነው አሉ።

    ትራምፕ ይህንን ምላሽ የሰጡት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲሆን

    “አስርት ዓመታት ወደ ኋላ የመለሰ ነው፤ በቅቷቸዋል። በገሃነም ውስጥ ነው ያለፉት፤ ከዚህ በኋላ ማድረግ የሚፈልጉት የመጨረሻው ነገር ኒውክሌር ማበልጸግ ነው” ብለዋል።

    “ያ ጥቃትም ጦርነቱን ጨርሶታል” ሲሉ አክለዋል።

    ትራምፕ አክለውም ኢራን የኒውክሌር ይዞታዎቿ ባይወድሙ ኖሮ የአገሪቱ መንግሥት የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ አይስማማም ነበር ብለዋል።

    ትራምፕ አሜሪካ የፈጸመችው ጥቃት የኢራን የኒውክሌር ይዞታዎችን ያወደመ ነው ሲሉ በድጋሜ ገልጸዋል።

    ሆኖም ጥቃቱ አሜሪካ በኢራን ላይ የፈጸመችው ጥቃት የኒውክሌር ማብላያ ይዞታዎችን እንዳላወደመ ሾልኮ የወጣ የአሜሪካ መከላከያ ማዕከል (ፔንታጎን) የደህንነት ግምገማ አሳይቷል።

    ቅድመ ግምገማው ጥቃቱ የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብር ምናልባትም በወራት ወደኋላ ሊመልሰው እንደሚችል ነው ያሳየው።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የኒውክሌር ቦምቦችን ለመስራት የሚያገለግለው “የመቀየሪያ ማዕከል” ወድሟል እንዲሁም ማየት አይቻልም ብለዋል።

    ሆኖም ሚኒስትሩ የትኛውን ይዞታ እንደሆነ አልጠቀሱም።

    “ከዚያ ተራራ ስር ያለው ነገር ሁሉ ውድመት ላይ ነው” በማለት ኢራን ከሳምንት በፊት ከነበረችበት የኒውክሌር መርሃ ግብሯ “ወደ ኋላ ቀርታለች” ብዋል።