ከአሜሪካ ጋር የሚተባበሩ አገራት "አደገኛ ምላሽ" እንደሚጠብቃቸው ኢራን አስታወቀች
አሜሪካ በኢራን ላይ ዳግም የከፈተችውን ጥቃት ተከትሎ ማክሰኞ ምሽት ሌላ ዙር ጥቃት ካደረሰች በኋላ ኢራን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ማዘዣ የአሜሪካ ወዳጅ የሆኑትን የአካባቢው አገራት አስጠነቀቀ።
ኻታም አል አንቢያ የሚባለው ኢራን ከአሜሪካ ጋር የምታካሂደውን ጦርነት የሚመዛው ዋና ማዘዣ አሜሪካ በደቡባዊ ኢራን ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ከአሜሪካ ጦር ጋር የሚተባበሩ የቀጣናው አገራት “አደገኛ ምላሽ ይጠብቃቸዋል” ሲሉ አስጠንቅቋል።
ዕዙ ዛሬ ረቡዕ ጠዋት በወጣው መግለጫ፣ የኢራን አብዮታዊ ዘብ እና የአገሪቱ ጦር ኃይል ለአሜሪካ ጥቃት አጸፋ መስጠቱን ጠቅሶ፣ በአካባቢው ባሉ የአሜሪካ ተቋማት እና ጦር ሰፈሮች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን አመልክቷል።
ጨምሮም የአሜሪካ ኃይሎችን የሚያስተናግዱ የአካባቢው አገራት “ከጥቃት ፈጻሚው የአሜሪካ ጦር ጋር የሚያደርጉት ትብብር የሚያስከትለውን አደገኛ ውጤት መቀበል አለባቸው” ብሏል።
አሜሪካ ማክሰኞ ምሽት በኢራን ደቡባዊ የባሕር ጠረፍ አካባቢዎች የአየር ጥቃት መፈጸም ከጀመረች ከአንድ ሰዓት በኋላ፣ የኢራን አብዮታዊ ዘብ እና ጦሩ በዮርዳኖስ፣ በባህሬን እና በኢራቅ የኤርቢል ከተማ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን በሚሳዔል እና በድሮን ማጥቃታቸውን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የኩዌት ጦር ኃይል ከኢራን በሚሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት የአገሪቱ የአየር መከላከያ ሥርዓቶች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ መደረጋቸው ተገልጿል።
በማክሰኞው ምሽት በሲሪክ አካባቢ በሚገኘው የኮህስታክ መንደር በተፈጸመ የአሜሪካ የአየር ጥቃት፣ በሰርግ ሥነ ሥርዓት ላይ የነበሩ ቢያንስ አምስት ሲቪሎች መገደላቸውን እና ከ60 በላይ ሰዎች መቁሰላቸው ተዘግቧል።
በኢራን መገናኛ ብዙኃን መረጃ መሠረት ከሟቾቹ መካከል አንድ ሕፃን ይገኛል፤ ከቆሰሉት አብዛኞቹም ከደህስታክ መንደር የሆኑ ሴቶች እና ሕፃናት ናቸው።