ቀጥታ, አሜሪካ እና ኢራን ስለቀጣዩ ዙር የሰላም ንግግር እየተወያዩ ባለበት የፓኪስታን ልዑካን ቴህራን ገቡ

አሜሪካ ከኢራን ጋር ስለ ሁለተኛ ዙር ድርድር እየተነጋገረች መሆኑን ቢቢሲ ማረጋገጥ ችሏል። ነገር ግን እስካሁን ድረስ ቀኑም ሆነ ቦታው አለመወሰኑ ተገልጿል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ኢራን ከስምምነት ለመድረስ ቁርጠኛ መሆኗን እስኪያረጋግጡ ድረስ የባሕር ኃይሉ የቴህራንን ወደቦችን ዘግቶ እንዲቆይ እንደሚፈልጉ ቢቢሲ መረዳት ችሏል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በሊባኖስ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 2,167 ደረሰ

    እስራኤል ረቡዕ ዕለት ከሊባኖስ የተወሰኑ አካባቢዎች "የአየር ድብደባ እየተፈጸመ ነው" በማለት ነዋሪዎች ለቅቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥታ ነበር

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የምስሉ መግለጫ, እስራኤል ረቡዕ ዕለት ከሊባኖስ የተወሰኑ አካባቢዎች "የአየር ድብደባ እየተፈጸመ ነው" በማለት ነዋሪዎች ለቅቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥታ ነበር

    እስራኤል በሊባኖስ የአየር ድብደባ ማድረግ ከጀመረች ጀምሮ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 2,167 መድረሱን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ። የሟቾች ቁጥር ማክሰኞ ዕለት ከተገለጸው በ43 ሰዎች ከፍ ማለቱ ተገልጿል።

    በእስራኤል ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም 7,061 ደርሰዋል።

    እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመችው ሦስት ተከታታይ ጥቃቶች ቢያንስ ሦስት የሕክምና ባለሙያዎች መገደላቸውን የሊባኖስ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

    ባለሥልጣናቱ እስራኤል ሆን ብላ የጤና ባለሙያዎችን ዒላማ ታደርጋለች ሲሉ ወንጅለዋታል።

    የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር የመጀመርያዎቹ የሕክምና ባለሙያዎች የተገደሉት በእስራኤል ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸውን ለማንሳት በሚጥሩበት ወቅት ነው ብሏል።

    በማስከተልም ሁለተኛ እና ሦስተኛ ቡድን ሲሄድም ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ሚኒስቴሩ ጨምሮ ገልጿል።

    የእስራኤል ጦር በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ቢጠየቅም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

    እስራኤል ሄዝቦላህ አምቡላንስን እና የሕክምና ተቋማትን ለወታደራዊ ዓላማዎች ይጠቀማል ስትል ማስረጃ ሳታቀርብ ትከስሳለች።

    የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር ግን ይህንን ውንጀላ ያስተባብላል።

    ሚኒስቴሩ እስራኤል በሊባኖስ ላይ ጥቃት መፈጸም ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ 91 የሕክምና ባለሙያዎች ሲገደሉ፣ 208 መጎዳታቸውን ገልጿል።

    አክሎም በሕክምና ተቋማት እና አምቡላንሶች ላይ ብቻ 120 ጥቃቶች መፈጸማቸውን አስታውቋል።

    ሚኒስቴሩ ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ የሚፈጸሙት ጥቃቶች “ጭካኔ የተሞላባቸው ወንጀሎች” ናቸው ብሏል።

    "የሕክምና ባለሙያዎች ቀጥተኛ ዒላማዎች ሆነዋል፣ ይህም . . . በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ የተደነገጉትን ሁሉንም ደንቦች እና መርሆዎች ሙሉ በሙሉ ችላ ማለቷን ያረጋግጣል” ብሏል።

    የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እስራኤል በሊባኖስ የፈጸመቻቸው አንዳንድ ድርጊቶች እንደ ጦር ወንጀል የሚታዩ ናቸው ብለዋል።

  2. ኢራን ከአሜሪካ ጋር ወደፊት ስለሚኖራት ንግግር ከፓኪስታን ጋር ከተወያየች በኋላ እንደምትወስን ተዘገበ

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ቅዳሜ ዕለት ፓኪስታን በደረሱበት ወቅት

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ቅዳሜ ዕለት ፓኪስታን በደረሱበት ወቅት

    ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ታስኒም የዜና ወኪል ቴህራን ከአሜሪካ ጋር የሚኖራትን ቀጣይ ድርድር ከፓኪስታን ልዑክ ጋር ከተወያየች በኋላ እንደምትወሰን ዘገበ።

    የዜና ኤጀንሲው “ስለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮችን” ጠቅሶ በቀጣዮ ዙር ውይይት ላይ ለመወሰን አሜሪካ እና እስራኤል ከሊባኖስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ከደረሱ “ለኢራን እንደ በጎ ምልክት” መሆኑን ተናግሯል።

    ይሁን እንጂ አሜሪካ "ምክንያታዊ የሆነ የድርድር ማዕቀፍን መከተል አለባት" ያሉት የዜና ኤጀንሲው ምንጮች "ከመጠን በላይ የተለጠጡ ፍላጎቶችን በማቅረብ ሂደቱን ማደናቀፍ" ወይም ከተኩስ አቁም በፊት የተደረጉትን ስምምነቶችን መጣስ እንደሌለባት ጨምረው ተናግረዋል።

    ታስኒም ዋሺንግተን ቀጣዩን ዙር ውይይት ለማካሄድ ፈቃደኛ መሆኗን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን መዘገባቸውን ጠቅሶ፣ ነገር ግን የኢራን የልዑካን ቡድኑ ዩኤስ "ምክንያታዊ ድርድርን ለመጀመር የሚያስፈልጉትን የተወሰኑ መርሆዎችን ማክበር" እንደሚያስፈልጋት አፅንዖት ሰጥተዋል ብሏል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ ከኢራን ጋር ስለ ሁለተኛ ዙር ድርድር እየተነጋገረች መሆኑን ቢቢሲ ማረጋገጥ ችሏል። ነገር ግን እስካሁን ድረስ ቀኑም ሆነ ቦታው አለመወሰኑ ተገልጿል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ኢራን ከስምምነት ለመድረስ ቁርጠኛ መሆኗን እስኪያረጋግጡ ድረስ የባሕር ኃይሉ የቴህራንን ወደቦችን ዘግቶ እንዲቆይ እንደሚፈልጉ ቢቢሲ መረዳት ችሏል።

  3. የፓኪስታን ልዑካን ቡድን ቴህራን ደረሰ

    የፓኪስታን ጦር አዛዥ አሲም ሙኒር ለኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰይድ አባስ አራግቺ ሰላምታ ሲሰጡ

    የፎቶው ባለመብት, Government of Iran

    የምስሉ መግለጫ, የፓኪስታን ጦር አዛዥ አሲም ሙኒር ለኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰይድ አባስ አራግቺ ሰላምታ ሲሰጡ

    አሜሪካን እና ቴህራንን እያሸማገለ የሚገኘው የፓኪስታን ልዑካን ቡድን ቴህራን ገባ።

    ከልዑካን ቡድኑ መካከል ከዚህ ቀደም ትራምፕ “የምወደው” ሲሉ የገለጿቸው ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር እና የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ሞሺን ናቅቪ እንደሚገኙበት በመንግሥታቱ ድርጅት የፓኪስታን ተልዕኮ መግለጫ ያስረዳል።

    ቀደም ሲል የኢራን መገናኛ ብዙኃን፣ ኢሪብ የዜና ወኪል የአሜሪካን መልዕክት ለማስተላለፍ እና ስለሁለተኛው ዙር ድርድር ለመነጋገር የልዑካን ቡድን ወደ ቴህራን እንደሚመጣ ዘግቦ ነበር።

    አሜሪካ እና ኢራን የመጀመርያውን ዙር ድርድር ባለፈው ሳምነት መጨረሻ ላይ በኢዝላማባድ ያደረጉ ሲሆን ያለምንም ውጤት ተጠናቅቋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሐማድ ሼህባዝ ሻሪፍ ሳዑዲ አረቢያ፣ ጂዳ ደርሰዋል።

    ጽህፈት ቤታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገራት የተጓዙት “በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ ለመለዋወጥ” መሆኑን ገልጿል።

  4. ምን ያህል መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል አለፉ?

    የነዳጅ ጫኝ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ የኢራን ወደቦችን ሰኞ ዕለት ከዘጋች ጀምሮ 15 መርከቦች የሆርሙዝ ወሽመጥን አቋርጠዋል።

    ከእነዚህ መካከል ደግሞ ዘጠኙ ከኢራን ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ቢቢሲ ቬሪፋይ የተመለከታቸው የመርከቦች እንቅስቃሴን የሚጠቁሙ መረጃዎች ጠቁመዋል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ (ሴንቲኮም) ወደ ኢራን ወደቦች የሚገቡም ሆነ የሚወጡ በሙሉ እገዳው ይመለከታቸዋል ብሏል።

    ከኢራን ወደቦች ውጪ የሚመጡም ሆነ የሚሄዱ መርከቦች ግን የመንቀሳቀስ ነጻነታቸው የተጠበቀ መሆኑን አክሏል።

    የመርከቦች እንቅስቀሴን መከታተያዎች ከኢራን ጋር ግንኙነት ያላቸው ስድስት መርከቦች በወሽመጡ በኩል ማለፋቸውን ያሳያሉ።

    የአሜሪካ ጦር በርካታ መርከቦች እንዲመለሱ ተደርገዋል ቢልም ቢቢሲ ከገለልተኛ ወገን ይህንን ማጣራት አልቻለም።

    ነገር ግን ቢያንስ አንድ መርከብ በወሽመጡ በኩል ሲያልፍ እንዲመለስ መደረጉን የመረጃ መከታተያዎቹ አሳይተዋል።

    በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለበት ሪች ስታሪ መርከብ ከዩኤኢው ሻርጃ ምሥራቃዊ ክፍል ተነስቶ በወሽመጡ በኩል ሲያልፍ እንዲመለስ የተደረገ ቢሆንም ረቡዕ ዕለት ግን በባህረ ሰላጤው እንዲያልፍ ተደርጓል።

    በተጨማሪም ሁለት የኢራንን ባንዲራ የሚያውለበልቡ መርከቦች እገዳው ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ ከኢራኑ ቻባሃራ ወደብ ተነስተው በሆርሙዝ ወሽመጥ ምሥራቃዊ ክፍል በኩል አልፈዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ወቅት ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ የሆርሙዝ ወሽመጥ “እየተከፈተ ነው” ብለዋል።

    የኢራን ጦር አዛዥ አሊ አብዶላህ እገዳው ካልተነሳ “ማንኛውም የወጪ እና ገቢ ንግድ በፐርዢያ ባሕረ ሰላጤ፣ በኦማን ባሕር እና በቀይ ባሕር” እንዳያልፍ እንደሚያደርጉ ዝተዋል።

    ትራምፕ ከዚህ ቀደም አሜሪካ የኢራንን ባሕር ኃይል ማውደሟን ተናግረው የነበረ ቢሆንም አሁንም ግን በቀጣናው የሚደረግ የባሕር ጉዞ ላይ አደጋ መደቀኑ አልቀረም።

  5. ፕሬዚዳንት ትራምፕ ስለኢራን ጦርነት የሚሰጡት እርስ በእርሱ የሚጣረሰው መልዕክት

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስለ ኢራኑ ጦርነት እና ስለሚያበቃበት መንገድ የሚናገሩት እርሱ በእርሱ የሚጣረስ ነው።

    ትራምፕ ከፎክስ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ላይ “የጦርነቱ ማብቂያ እየተቃረበ ነው” ብለዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም ተስማምተው ድርድር ጀምረዋል።

    ትራምፕ ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለምልልስ ላይ ተጨማሪ የአየር ድብደባዎች ሊፈጸሙ እንደሚችሉም ተናግረዋል።

    “የአየር ድብደባውን አሁን ባቆም፤ አገሪቱን መልሶ ለመገንባት 20 ዓመት ይወስድባቸዋል፤ እና ደግሞ ገና አልጨረስንም” ሲሉ አክለዋል።

    “ምን እንደሚሆን እናያለን። ከስምምነት ለመድረስ በጣም የሚፈልጉ ይመስለኛል።”

    ትራምፕ የሁለት ሳምንቱ የተኩስ አቁም ይራዘም እንደሆን ሲጠየቁም እንዲሁ እርስ በእርሱ የሚጣረስ ምላሽ ሰጥተዋል።

    የፈረንሳይ የዜና ወኪል ግን አደራዳሪዎች የሁለት ሳምንቱ የተኩስ አቁም እንዲራዘም ለማድረግ እየተቃረቡ መሆኑን ዘግቧል።

    አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን ደግሞ “አሜሪካ በይፋ የተኩስ አቁሙን ለማራዘም አልተስማማችል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    “ዩኤስ እና ኢራን ከስምምነት ላይ ለመድረስ እየተነጋገሩ ነው” ሲሉም አክለዋል።

  6. አሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁሙን ለማራዘም እየተነጋገሩ ነው- ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን

    የአሜሪካ እና ኢራን ባንዲራዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለሁለት ሳምንት የተቀመጠውን የተኩስ አቁም ለማራዘም ከኢራን ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ተናገሩ።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት የሚያበቃው የሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ሚያዝያ 14 2018 ዓ.ም. ነው።

    ባለሥልጣኑ “አሜሪካ የተኩስ አቁሙን ለማራዘም በይፋ አልተስማማችም” ሲሉ ተናግረዋል።

    “ከስምምነት ላይ ለመድረስ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ንግግር ቀጥሏል” ሲሉ አክለዋል።

    ቀድም ሲል ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የኢራን መገናኛ ብዙኃንን ጠቅሶ የተኩስ አቁም መራዘሙ አልተረጋገጠም ብሎ ነበር።

  7. ኢራን ከአሜሪካ ጋር መልዕክት መለዋወጥ መቀጠሏን ተናገረች

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ በቴህራን እና ዋሺንግተን መካከል የሚደረገው የመልዕክት ልውውጥ በአደራዳሪዋ ፓኪስታን በኩል “እንደቀጠለ መሆኑን” ተናገሩ።

    ባጋይ የኢራን አቋም “በቀጠለው ንግግር በግልጽ የተቀመጠ እና በድጋሚ የተገለጸ ነው” ብለዋል።

    አክለውም ኢራን ዛሬ “ምናልባትም” የፓሰኪስታን ልዑካንን ተቀብላ እንደምታስተናግድ ተናግረዋል።

    ልዑካኑ በኢዝላማባድ የተጀመረው ድርድር ቀጣይ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር እና “በኢራን እና አሜሪካ አቋሞች ላይ በዝርዝር ለመነጋገር” እንደሆነ አብራርተዋል።

    ባጋይ አሜሪካ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መታጠቅ ትፈልጋለች ስትል የምታቀርበውን ክስ ውድቅ አድርገው የኒውክሌር ፕሮግራሟ “ሰላማዊ ነው” ብለዋል።

    ባጋይ “በፍላጎቶቿ ላይ በመመስረት [ዩራኒየም] ማበልጸጓን መቀጠል ይኖርባታል” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

    ነገር ግን በማበልጸጉ ደረጃ እና ዓይነት ዙሪያ የመነጋገር ዕድል ሊኖር ይችላል” ብለዋል።

  8. ትራምፕ ቻይና ለኢራን ጦር መሣሪያ ላለመላክ ተስማምታለች አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለቻይናው አቻቸው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ከጻፉ በኋላ “ለኢራን ጦር መሣሪያ ላለመላክ” መስማማታቸውን ተናገሩ።

    ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ “ቻይና የሆርሙዝ ወሽመጥን በቋሚነት በመክፈቴ ደስተኛ ናት። ይህንን የማደርገው ለእነርሱ ነው። እና ለመላው ዓለም” ሲሉ ጽፈዋል።

    “እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ዳግመኛ አይከሰትም። ለኢራን ጦር መሣሪያ ላለመላክ ተስማምተዋል” ሲሉ አክለዋል።

    “በብልሃት፣ በጥሩ ሁኔታ በጋራ እየሰራን ነው!! ያ ታዲያ ጦርነትን እንድናሸንፍ አያደርግም??? ነገር ግን አስታውሱ በመዋጋት ረገድ በጣም ጎበዞች ነን፤ መሆን ካለበት ከማንም በበለጠ [እንዋጋለን]!!!”

    ማክሰኞ ዕለት ቻይና የአሜሪካ ጦር የኢራንን ወደብ ለመዝጋት የወሰደው እርምጃ “ኃላፊት የጎደለው ነው” በማለት ኮንና የተኩስ አቁሙን “አደጋ ላይ ይጥላል” ብላ ነበር።

    አሜሪካ የኢራንን ወደቦችን ከዘጋች በኋላ በወሽመጡ በኩል ካለፉ ጥቂት መርከቦች መካከል የቻይና አንዱ ነው።

    የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማክሰኞ ዕለት በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ቻይና ለኢራን የአየር መቃወሚያ ለመስጠት እየተዘጋጀች ነው የሚለውን ዘገባ “ሙሉ በሙሉ የፈጠራ ወሬ” ሲሉ አጣጥለውታል።

  9. በሲሪላንካ ለመቆየት የተገደዱት ከ200 በላይ የኢራን ባሕርተኞች ወደ አገራቸው ተመለሱ

    የኢራን ጦር መርከብ የሆነችው አይሪስ ዴና በቤንጋል የባሕር ዳርቻ ታይታ ነበር

    የፎቶው ባለመብት, AP

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ጦር መርከብ የሆነችው አይሪስ ዴና በቤንጋል የባሕር ዳርቻ ታይታ ነበር

    በአሜሪካ ጦር ጥቃት ተፈፅሞባቸው ከአንድ ወር በላይ ሲሪላንካ እንቆዩ የተገደዱ ከ200 በላይ የኢራን ባህርተኞች አገራቸው ገቡ።

    የሲሪላንካ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ከአይሪስ ዴና ከምትባለው መርከብ 32 ባሕርተኞች እና አይሪንስ ቡሺሂር ከተባለችው መርከብ ደግሞ 206 ባሕርተኞች አገሪቱን ለቀው መውጣታቸውን አስታውቀዋል።

    የኢራን የጦር መርከብ የሆነችው አይሪስ ዴና ባለፈው ወር በአሜሪካ ሰርጓጅ መርከብ ከተመታች በኋላ 104 ባሕርተኞች ሲገደሉ፤ መርከቧ ደግሞ ከሲሪላንካ የባሕር ዳርቻ 40 ኪሎ ሜትር ላይ ሰምጣለች።

    ከዚህ ጥቃት ማግስት ደግሞ የሞተር ብልሽት የገጠማት አይሪንስ ቡሺሂር ተባለችው መርከብ በሲሪላንካ ፈቃድ ወደብ ላይ እንድትቆይ ተደርጓል።

    ምክትል ሚኒስትሩ ለሮይተርስ የዜና ወኪል የሁለቱም መርከቦች ባሕርተኞች ማክሰኞ ዕለት ወደ ኢራን መጓዛቸውን አረጋግጠዋል።

    በጥቃቱ የተገደሉ የ84 ኢራናዊያን ባሕርተኞች አስከሬን በቴህራን አመቻችነት ወደ ኢራን መመለሱ ይታወሳል።

    የመርከቡ ጥቃት አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ጦርነት በከፈቱ በቀናት ውስጥ የተፈፀመ ሲሆን፤ ጥቃቱ የጦርነቱን ዓውድ እንዲሰፋ አድርጎታል።

  10. ኢራን የአሜሪካ የወደብ መዝጋት የሚቀጥል ከሆነ በባሕረ ሰላጤው፣ ቀይ ባሕር እና በኦማን የባሕር ወሽመጥ እርምጃ እወስዳለሁ ስትል ዛተች

    በኢራን የተለጠፈ ፖስተር

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የኢራን የካተን አል አብቢያን አዛዥ አሊ አብዶላሂ አሜሪካ እገዳዋን የምትቀጥል እንዲሁም “ለኢራን የንግድ እና የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ደኅንነት ስጋት የምትሆን ከሆነ” “የተኩስ አቁም ስምምነቱን የመጣስ የመጀመርያ እርምጃ” ይሆናል ብለዋል።

    የኢራን ኃይሎች “በፋርስ ባሕረ ሰላጤ፣ በኦማን ባሕር እና በቀይ ባሕር ማንኛውም የገቢ እና ወጪ ንግድ ምርቶች” መንቀሳቀሳቸውን እንዳይቀጥሉ እንደሚያደርጉ አክለው ተናግረዋል።

    አብዶላሂ የትኞቹ አገራት የወጪ እና ገቢ ንግዳቸው እንደሚጎዳ ያልገለጹ ሲሆን የጠቀሱት የባሕር ክፍል ግን ሰፊ አካባቢን ይሸፍናል።

    አሜሪካ የኢራን ወደቦችን የዘጋችው ከሰኞ ዕለት ጀምራ ነው።

    ረቡዕ ዕለት የአሜሪካ ጦር በ24 ሰዓታት ውስጥ “አንድም መርከብ እገዳውን አልፎ አልሄደም” ሲል አስታውቋል።

    በኦማን ባሕረ ሰላጤ ስድስት የንግድ መርከቦች እንዲመለሱ መደረጋቸውን ጨምሮ አስታውቋል።

    በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተደረገው የመጀመርያ ዙር ድርድር ያለውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ ቀጣዩ ዙር በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ሊጀመር እንደሚችል ትራምፕ አስታውቀዋል።

    ኢራን ግን እስካሁን ድረስ ድርድሩ ስለመደረጉ ያለችው ነገር የለም።

  11. የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ “ጠንካራ እርምጃ” እየወሰደ መሆኑን ገለጸ

    የእስራኤል ጦር ከሊባኖስ ጋር በሚዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ የአየር ድብደባ እየፈጸመ ይገኛል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ጦር አገሪቱ ከሊባኖስ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ የአየር ድብደባ እየፈጸመ ይገኛል

    የእስራኤል መከላከያ በደቡባዊ ሊባኖስ "የአየር ድብደባ እያካሄደ" መሆኑን በመግለፅ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጠ፥።

    ጦሩ በዛሃራኒ ወንዝ ደቡባዊ አቅጣጫ “ከባድ እርምጃ” እየወሰደ መሆኑን ገልጾ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ አስጠንቅቋል።

    “በሄዝቦላህ አካባቢ የሚገኝ ማንኛውም አካል፤ በተቋማቸው ወይም የውጊያ ተሽከርካሪዎቻቸው አካባቢ፣ ሕይወቱን ለአደጋ ያጋልጣል” ሲል ባወጣው መግለጫ ላይ ጠቅሷል።

    እስራኤል እና ሊባኖስ ማክሰኞ ዕለት ከተነጋገሩ በኋላ ወደፊት በሚገለጽ ጊዜ እና ቦታ በቀጥታ ድርድር ለመጀመር መስማማታቸውን ተገልጿል።

    እስራኤል በበኩሏ በሊባኖስ የሚንቀሳቀሱ ሁሉንም መንግሥታዊ ያልሆኑ የሽብር ቡድኖችን ትጥቅ ማስፈታት እንደምትፈልግ ተናግራለች። ይህም የሄዝቦላህ ታጣቂዎችን ለማመልክት የተጠቀመችበት ነው።

    ሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ እና የሰብአዊ ቀውሷን ለመፍታት እርምጃዎችን እንድትወስድ ጥሪ አቅርባለች።

    እስራኤል ግን ከዛሬ ማለዳ ጀምራ በሊባኖስ የአየር ድብደባ እያካሄደች መሆኑን የሚወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ።

  12. ፕሬዝዳንት ፐዝሽኪያን ኢራንን ለማንበርከክ የሚደረግ ሙከራ እንደሚከሽፍ ተናገሩ

    የኢራን ፕሬዝዳንት መሱድ ፐዝሽኪያን

    የፎቶው ባለመብት, Iranian Presidency handout via Getty Images

    የኢራን ፕሬዝዳንት መሱድ ፐዝሽኪያን አሜሪካ እና እስራኤል ኢራንን በኃይል “ለማንበርከክ” የሚያደርጉት ማንኛውም ሙከራ እንደሚከሽፍ እና ቴህራን እንዲህ ዓይነት አማራጮችን መቼም እንደማትቀበል ተናገሩ።

    ከኢራን የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ባለሥልጣናት ጋር የተነጋገሩት ፕሬዝዳንት ፐዝሽኪያን ቴህራን ጦርነት አሊያም አለመረጋጋትን አትፈልግም ብለዋል።

    በአንፃሩ “[ኢራን] ሁሌም ቢሆን ገንቢ ውይይቶች እና ከተለያዩ አገራት ጋር የመነጋገር አስፈላጊነትን ደጋግማ ገልፃለች” ሲሉም አክለዋል።

    በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን የተላለፈው የፕሬዝዳንቱ ንግግር፤ ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ እና ኢራን ንግግር በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት በፓኪስታን ኢዝላማባድ ይጀምራል ካሉ በኋላ የተሰማ ነው።

    በቅርብ ይጀመራል ስለተባለው ሁለተኛ ዙር ንግግር ቴህራን እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።

  13. የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ከአሜሪካ እና ኢራን የኢዝላማባድ ንግግር በኋላ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር እና ቱርክን ለመጎብኘት አቀኑ

    ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሻሪፍ

    የፎቶው ባለመብት, Reuter

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በኢራን ጉዳይ ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላይ ሚኒስትር ሻሪፍን አነጋግረዋል

    የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሻባዝ ሻሪፍ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትን እና ቱርክን ለመጎብኘት የአራት ቀን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት መጀመራቸውን የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳዑዲ አረቢያ እና ኳታርን እንደሚጎበኙም ተገልጿል።

    ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የመጣው ኢዝላማባድ ሁለተኛ ዙር የአሜሪካ እና ኢራንን የሰላም ንግግር ለማዘጋጀት እየተሰናዳች ባለችበት ጊዜ ነው።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት ለኒው ዮርክ ፖስት ጋዜጠኛ “በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ በኢዝላማባድ የሆነ ነገር ይከሰት ይሆናል” ብለዋል።

    የጠቅላይ ሚኒስትር ሻቲፍ የሳዑዲ አረቢያ እና ኳታር ጉብኝት “በሁለትዮሽ አውድ” እንደሚካሄድ የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቱርክ በአንታላያ የዲፕሎማሲ ፎረም የሚሳተፉ ሲሆን፤ ከፎረሙ ጎን ለጎን ከቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲጵ ጣይፕ ኤርዶጋን እና ከሌሎች መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

  14. ትራምፕ የካቶሊኩ ርዕሳነ ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ሊዮ ላይ የሚሰነዝሩትን ትችት ቀጥለዋል

    ፖፕ ሊዮ 14ተኛ እና ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በካቶሊክ ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳስ ፖፕ ሊዮ 14ተኛ ላይ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ የትትስር ገፅ ‘ኢራን 42 ሺህ ንፁሃንን እንደገደለች እባካችሁ ንገሯቸው’ በማለት ሰሞነኛ ትችታቸውን ቀጠሉ።

    “እባካችሁ አንድ ሠው ለፖፕ ሊዮ ኢራን ባለፉት ሁለት ወራት 42 ሺህ ምንም ያልታጠቁ፣ ተቃዋሚ፣ ንፁኃንን ገድላለች፤ ኢራን የኒውክሌር ቦምብ ባለቤት መሆኗ በፍፁም ተቀባይነት የለውም ብላችሁ ንገሯቸው” ብለዋል።

    “ለጉዳዩ ትኩረት ስለሰጡት እናመሰግናለን። አሜሪካ ተመልሳለች” ሲሉም የትችት ጽሑፋቸውን አሳርገዋል።

    ፖፕ ሊዮ ስለ ኢራን ጦርነት አስተያየት ከሰጡ በኋላ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለጋዜጠኞች የርዕሳነ ሊቀ ጳጳሱ “አድናቂ” እንዳልሆኑ በመግለፅ፤ “ወንጀል ላይ ደካማ እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የማይችሉ” ሲሉ ተችተዋቸዋል።

    ፖፕ ሊዮ በበኩላቸው የትራምፕ አስተዳደር ላይ “ፍርሃት” እንደሌላቸው እና ለመናገር ወደ ኋላ እንደማይሉ ገልፀዋል።

    ትራምፕ ቱሩዝ ሶሾል በተባለው ማኅበራዊ የትስስር ገፃው ላይ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) በሚመለከት ጽሑፍ ያጋሩ ሲሆን፤ “ኔቶ [እርዳታ በጠየቅን ጊዜ] ከእኛ ጋር አልነበረም፤ እናም በቀጣይም ከእኛ ጋር አይሆኑም” ብለዋል።

  15. ከእስራኤል እና ሊባኖስ የዋሽንግተን ንግግር በኋላ እስራኤል ሄዝቦላህን ማጥቃቷን ቀጠለች

    በሊባኖስ የወደሙ ሕንፃዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በደቡባዊ ሊባኖስ እስራኤል ማክሰኞ ዕለት በፈፀመችው ጥቃት ሕንፃዎች ወድመዋል

    እስራኤል እና ሊባኖስ ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ንግግር ካደረጉ ከአንድ ቀን በኋላ የእስራኤል ጦር ሊባኖስን ማጥቃቱን ቀጠለ።

    እስራኤል በንግግሩ ያልታሳተፈውን ሄዝቦላህን በመጠቆም መንግሥታዊ ያልሆኑ የሽብር ቡድኖችን ትጥቅ ማስፈታት እንደምትፈልግ ገልፃለች።

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል (አይዲኤፍ) ባለፉት ጥቂት ቀናት ሄዝቦላህ የሽብር እና ወታደራዊ መሠረተ ልማቶችን መምታቱን አስታውቋል። ጦሩ “በሄዝቦላህ የሽብር ቡድን ላይ ጥቃት መፈፀም እንቀጥላለን” ብሏል።

    ትናንት ረቡዕ በዋሽንግተን የተደረገውን የእስራኤል-ሊባኖስ ንግግርን በማስመልከት አሜሪካ ባወጣችው መግለጫ አገራቱን ለታሪካዊ ምዕራፍ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት በቀጣይ ንግግሮች እንዲደረጉ ድጋፏን እንደምትቀጥል ገልፃለች።

    “የሊባኖስ መንግሥት የኃይሉን ብቸኝነት ለመመለስ ለያዘው ዕቅድ እና የኢራንን ከመጠን ያለፈ ተፅዕኖ ለመቋጨት” ዋሽንግተን ድጋፍ እንደምታደርግም ጠቅሳለች።

  16. አሜሪካ የኢራን ወደቦችን በዘጋች በቀናት ውስጥ በሁለቱ አገራት መካከል ሁለተኛ ዙር ንግግር በቅርቡ ሊካሄድ ነው

    ባሕር ላይ ያለ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የተከሰቱ አዲስ ሁነቶች፡

    • የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የገቡትን ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረው ንግግር በዚህ ሳምንት ሊጀምር እንደሚችል ጠቁመዋል።
    • የኢራን መገናኛ ብዙኃን ኢርና ግን ዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ ስለውይይቱ "ምንም መረጃ" እንደሌለ ዘግቧል። ሆኖም የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ንግግሮች ዳግም ሊጀመሩ የሚችሉበት ከፍተኛ ዕድል እንዳለ ተናግረዋል።
    • በአሜሪካ የሊባኖስ አምባሳደር በአገራቸው እና በእስራኤል መካከል በዋሽንግተን የተደረገውን የመጀመሪያ ንግግር “ፍሬያማ” ብለውታል። በአሜሪካ የእስራኤል አምባሳደር ደግሞ ንግግሩ ሦስቱ አገራት “ተመሳሳይ ገፅ ላይ መሆናቸውን” ያሳየ ነው ብለዋል።
    • አሜሪካ ኢራን ወደቦች ላይ የጣለችው የእንቅስቃሴ እግድ ተግባራዊነቱ የቀጠለ ሲሆን፤ አሜሪካ የኢራን ነዳጅ ላይ ሙሉ ማዕቀብ እንደምትጥል አስታውቃለች። እርምጃው አሜሪካ እና ኢራን በፓኪስታን ያደረጉት የሰላም ድርድር ያለ ውጤት በመጠናቀቁ የተወሰደ ነው።
    • አሜሪካ በመጀመሪያዎቹ 24 ሰዓታት ውስጥ ከኢራን ወደቦች እና የባሕር ዳርቻዎች ምንም ዓይነት መርከቦች እንዳላለፉ ገልፃለች። በቢቢሲ የተረጋገጠው የመርከቦች መረጃ እግዱ ከጀመረ በኋላ ከኢራን ጋር ግንኙነት ያላቸው አራት መርከቦች የሆርሙዝ ወሽመጥን ማለፋቸውን አሳይቷል።
    • የአሜሪካ እግድ በሚቀጥለው ሳምንት የሚያበቃው የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት በታወጀበት ወቅት የተጣለ ነው። ኢራን የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ሆርሙዝ ወሽመጥን ዘግታለች።
  17. የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር 'ትልቅ ስምምነት' ማድረግ እንደሚፈልጉ ተናገሩ

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ፣ ትራምፕ ከኢራን ጋር “ትልቅ ስምምነት” ማድረግ እንደሚፈልጉ መናገራቸውን የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።

    ቫንስ በአቴንስ፣ ጆርጂያ በተካሄደው የተርኒንግ ፖይንት ዩኤስኤ ዝግጅት ላይ ለታዳሚዎቹ እንደተናገሩት በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በፓኪስታን የተካሄደው ድርድር "እጅግ በጣም ብዙ እድገት አሳይቷል" ብለዋል።

    ነገር ግን ትራምፕ ከኢራን ጋር "ትንሽ ስምምነት" እንደማይፈልጉ እና በምትኩ "ትራምፕ ታላቅ ስምምነት" ለማድረግ እንደሚፈልጉ ሲቢኤስ ዘግቧል።

    ቫንስ በሁለቱ አገሮች መካከል ከፍተኛ አለመተማመን እንደነበር ተናግረዋል።

    አክለውም "ያንን ችግር በአንድ ጀምበር መፍታት አትችሉም" ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

  18. ትራምፕ የኢራን ጦርነት “ሊያበቃ ተቃርቧል” አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የጀመሩት ጦርነት “ሊያበቃ ተቃርቧል” ሲሉ ለፎክስ ኒውስ ተናገሩ።

    ትራምፕ ለፎክስ ኒውስ የሰጡት ቃለ ምልልስ የሚተላለፈው 7፡00 ላይ ቢሆንም በማስታወቂያው ላይ ግን ጦርነቱ “ሊያበቃ የተቃረበ ይመስለኛል” ሲሉ ተደምጠዋል።

    ትራምፕ ይህንን ያሉት በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ከኢራን ጋር ኢዝላማባድ ተገናኝተው የተጀመረውን ውይይት እንደሚቀጥሉ ከተናገሩ በኋላ ነው።

    ፎክስ ኒውስ ኦንላይን በማህበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ በለቀቀው የቃለ ምልልሱ ማስታወቂያ ላይ ትራምፕን ጦርነቱ አብቅቶ እንደሆነ ጠይቋቸዋል።

    “ሊያበቃ የተቃረበ ይመስለኛል። አዎ” ሲሉ መልሰዋል። “እኔ እንደማየው በጣም ሊያበቃ መቃረቡን ነው” ብለዋል።

  19. ትራምፕ አሜሪካ እና ኢራን “በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ” ሊወያዩ እንደሚችሉ ተናገሩ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል “በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ” ንግግር ሊጀመር እንደሚችል ለኒውዮርክ ፖስት ተናገሩ።

    “በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ የሆነ ነገር ሊከሰት ይችላል። እና እኛ የበለጠ ወደዚያ [ፓኪስታን] የመሄድ ዝንባሌ አለን” ማለታቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።

    ሁለቱ አገራት የተኩስ አቁም ከደረሱ በኋላ በፓኪስታን ተገናኝተው ለረዥም ሰዓት የተወያዩት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ነበር።

    በወቅቱ የአሜሪካን ልዑክ የመሩት ምክትል ፕሬዜዳንቱ ጄዲ ቫንስ ሲሆኑ የኢራን ልዑክ ደግሞ የተመራው በአፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባገር ጋሊባፍ ነበር።

    ነገር ግን ውይይቱ ያለምንም ስምምነት ተቋጭቷል።

    ዛሬ የኢራን መገናኛ ብዙኃን በፓኪስታን እና ቴህራን መካከል የመልዕክተት ልውውጥ መኖሩን ዘግበው ከአሜሪካ ጋር ቀጣይ ውይይት ለማድረግ ስምምነት ስለመደረሱ ግን “ምንም መረጃ የለም” ብለው ነበር።

  20. የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ውይይቱ “የመጨረሻው መጀመሪያ” ይሆናል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናገሩ

    የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን አገራቸው ከእስራኤል ጋር የምታደርገው ውይይት የስቃይዋ “የመጨረሻው መጀመሪያ” ይሆናል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናገሩ።

    እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ “ወረራዋን በመቀጠሏ” መረጋጋት “እንደማይመለስ” ጨምረው ተናግረዋል።

    የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ የደህንነት ቀጠና ለመገንባት በሚል ወታደራዊ ዘመቻ እያካሄደ ነው።

    ጦርነቱ ካበቃም በኋላ የእስራኤል ጦር መሬቱን በወረራ ይዞ ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት በብዙዎች ዘንድ ተፈጥሯል።

    ከአስርት ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የእስራኤል እና ሊባኖስ አምባሳደሮች በአሜሪካ ተገናኝተው ውይይታቸውን ጀምረዋል።

    ሁለቱ አገራት ምንም ዓይነት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የላቸውም።

    ይህ ውይይት እስራኤል የሄዝቦላህ ወታደራዊ ይዞታዎች ናቸው በሚል የምትፈጽመውን ድብደባ ያስቆማል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

    እስራኤል፣ አሜሪካ እና በርካታ ሊባኖሳውያን ሄዝቦላህ ትጥቅ እንዲፈታ ይፈልጋሉ። ነገር ግን በቤይሩት የሚገኘው መንግሥት ይህንን ያለ ሄዝቦላህ ይሁንታ ማስፈጸም አይችልም።

    ነገር ግን የእስራኤል ጥቃትም ቢሆን ግጭቱን ከማባባስ ባሻገር ዘላቂ መፍትሄ ስለማምጣቱ ማንም እርግጠኛ አይደለም።

    የሄዝቦላህ ደጋፊዎች የታጠቃቸው የጦር መሣሪያዎች ራሱን ከእስራኤል ጥቃት የሚከላከልበት ነው የሚሉ ሲሆን ቡድኑም ቢሆን በየትኛወም ውሳኔ እንደማይገዛ አስታውቋል።