የሰዓት እላፊ ገደቦችን ተከትሎ የፈረንሳይ ከተሞች ሌሊቱን በሰላም ማደራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፁ
ቅዳሜ እና እሑድ በመላ አገሪቱ የተከሰተውን ሁከትና ዘረፋ ተከትሎ በበርካታ የፈረንሳይ ከተሞች ውስጥ የተጣሉ የሰዓት እላፊ ገደቦች፣ ሌሊቱ በአንጻራዊ ሰላም እንዲያልፍ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሴባስቲያን ለኮርኑ ተናገሩ።
ተቃዋሚዎች ቅዳሜ እና እሁድ ተሰባስበውበት የነበረውን ፕላስ ደ ላ ሬፑብሊክ እና የሌይ አል የገበያ አካባቢን ጨምሮ፣ በማዕከላዊ ፓሪስ በሚገኙ የተወሰኑ አካባቢዎች የሰዓት እላፊ ገደቦች ተጥለዋል።
በደቡባዊ ፈረንሳይ በሚገኙት ማርሴይ፣ ቦርዶ፣ ኒስ እና ሊዮንን ጨምሮ በሰሜኖቹ ሊልና ሌሎች ከተሞች፣ የወጣቶችን እንቅስቃሴና መሰባሰብ የሚገድቡ ሌሎች እርምጃዎችም ተግባራዊ ሆነዋል።
የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ለኮርኑ እርምጃዎቹን ላስፈፀሙ የፖሊስ አባላት ምስጋና አቅርበው፣ ማክሰኞ ምሽት ተጨማሪ የሰዓት እላፊ ገደብ የሚጣሉባቸው ቦታዎች ጉዳይ እንደ አስፈላጊነቱ እንደሚወሰን ገልፀዋል።
ለኮርኑ በኤክስ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ ውሳኔዎቹ በየአካባቢው ባለው ሁኔታ መሠረት በፈረንሳይ የክልል ባለሥልጣናትና በአካባቢ ከንቲባዎች እንደሚወሰኑ አስገንዝበዋል።
ቅዳሜ እና እሁድ በነበረው ሁከት በርካታ ንብረት የተዘረፈ እና የወደመ ሲሆን ከ2,500 በላይ ሰዎች ታስረዋል። ወደ 1,000 የሚጠጉ የፖሊስ አባላትም ቆስለዋል።