ሐማስ ጥቃት ፈጽሞ እስራኤል ጋዛ ላይ የአየር ድብደባ ከጀመረች አንድ ሳምንት ሆነ

ልክ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ማለዳ ሐማስ በእስራኤል ላይ በፈጸመው የተቀናጀ ጥቃት የተጀመረው ግጭት ተባብሶ ቀጥሏል። ባለፉት ሰባት ቀናት እስራኤል በጋዛ ላይ ቀን አና ሌሊት ያለተቋረጠ የአየር ድብደባ አየፈጸመቸ ሲሆን፣ ሐማስም ወደ እስራኤል ሮኬቶቸን ሲተኩሰ ቆይቷል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የእስራኤል እና ፍልስጤማውያን ፍጥጫ እና ጦርነት መነሻ ምንድን ነው?

  2. እስራኤል የምትመካበት የሚሳኤል እና የሮኬቶች ማምከኛ ‘አይረን ዶም’ ምንድን ነው?

  3. በሞት ጥላ ስር ሆነው እስራኤልን እንቅልፍ የነሷት የሐማስ መሪዎች እነማን ናቸው?

  4. ሐማስ ባለፈው ሳምንት የሞከረው የእስራኤል ወረራ እንዲያበቃ ለማድረግ ነው፡ የሐማስ ባለሥልጣን

    የቀድሞው የሐማስ መሪ እና የአሁኑ የቡድኑ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ኻሊድ ሜሻል ታጣቂዎቻቸው ባለፈው ሳምንት የፈጸሙት “የእሰራኤል ወረራ እንዲያበቃ የተደረገ ሙከራ ነው” በማለት በዚህም “ኩራት” እንደሚሰማቸው ተናገሩ።

    የሐማስ የውጭ ጉዳይ ኃላፊው ሜሻል ለአንድ የቱርክ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ግጭቱ ባለፈው ሳምንት ሳይሆን በ1948 ነው የተጀመረው ብለዋል።

    “እስራኤል ሠራዊቷ ጠንካራ የማይበገር ነው ስትል ቆይታለች። በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ሲሸነፉ ስንመለከት እኛም ተደንቀናል” በማለት ባለፈው ሳምንት ሐማስ የፈጸመውን ጥቃት ጠቅሰዋል።

    ሐማስ በሰላማዊ ሰዎች፣ በሕጻናት እና በአረጋውያን ላይ ጥቃት ስለመፈጸሙ ሲጠየቁም “ያንን እንዳያደርጉ ስንነግራቸው ቆይተዋል፤ ነገር ግን በጦርነት ጊዜ እንዲህ አይነት ክስተቶች ያጋጥማሉ። እስራኤላውያንም ሰላማዊ ሰዎችን ሆን ብለው እንደማይገድሉ አይደል የሚናገሩት?” ሲሉ ጠይቀዋል።

    ሐማስ እስራኤል ሰላማዊ ሰዎችን ትገድላለች እያለ ሲከስ ቆይቶ ተመሳሳዩን ስለመፈጸሙ ሲጠየቁም በሁለቱ መካከል “ትልቅ ልዩነት” አለ በማለት መልሰዋል።

    “እኛ የዚያ መሬት ባለቤቶች ነን። ታዲያ ጠላት ከውጪ ሲመጣ ወታደር ሆነ ሰላማዊ ሰው ሁሉም ጠላት ናቸው። ወደ መሬቱ [ለወረራ] የመጣ ምንም ቢሆን ጠላት እና ጥፋተኛ ነው” ብለዋል።

  5. ፍልስጥኤማውያንን የሚደግፍ ሰልፍ ለንደን ውስጥ እየተካሄደ ነው

    ፍልስጥኤማውያንን የሚደግፍ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የተሳተፈበት ሰልፍ በዩናይትድ ኪንግደም ዋና ከተማ ለንደን ውስጥ እየተካሄደ ነው።

    ሰልፈኞቹ ማዕከላዊ ለንደን ከሚገኘው ከቢቢሲ ዋና መሥሪያ ቤት ውጪ የተሰባሰቡ ሲሆን፣ ቁጥራቸው እየጨመረ እጅግ በርካታ ሆነዋል።

    ሕጻናትን ጨምሮ በተለያዩ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች እየተሳተፉበት ያለው ይህ ሰልፍ፣ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት መቀመጫ ወደ ሆነው የለንደን ክፍል እንደሚያመሩ ተገልጿል።

    ከሰልፈኞቹ መካከል ትልቅ የፍልስጥኤም ሰንደቅ ዓላማ የያዙ ሰዎች የሚታዩ ሲሆን፣ ተሳታፊዎቹ “ፍልስጥኤም ነጻ ትውጣ፣ ወረራ ወንጀል ነው” የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ፣ ሌሎች ደግሞ “እስራኤልን ማስታጠቅ ይቁም” የሚሉ መፈክሮች የተጻፈባቸው ሰሌዳዎችን ይዘዋል።

  6. የሩሲያው ባለሥልጣን የሐማስ ተወካዮችን ለማናገር አቅደዋል

    የሩሲያው ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የታገቱ እስራኤላውያን መለቀቅን በተመለከተ ኳታር ውስጥ ከሐማስ ተወካዮች ጋር ለመገናኘት ማቀዳቸውን የሩሲያ መንግሥታዊ የዜና ወኪል ሪያ-ኖቮስቲ ዘገበ።

    ከሐማስ እና ታጣቂ ቡድኑን ትደግፋለች ተብላ ስሟ ከሚነሳው ኢራን ጋር ግንኙነት እንዳላት የሚነገረው ሩሲያ፣ በሐማስ እና በእስራኤል መካከል አሸማጋይ ሆና ለመቅረብ ጥረት እያደረገች ነው።

    ዛሬ ቅዳሜ በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በተካሄደ ስብሰባ ላይ እርዳታ ለማቅረብ እንዲቻል ተኩስ እንዲቆም የሚጠይቅ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ አቅርባለች።

    የሩሲያው ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚኻይል ቦግዳኖቭ ለሪያ-ኖቮስቲ ዜና ወኪል እንደተናገሩት፣ ወደ ኳታር በሚያደርጉት ጉዞ የሐማስ ተወካዮች “ፈቃደኛ ከሆኑ አግኝተው ለመነጋገር ፈቃደኛ” መሆናቸውን ገልጸዋል።

    “በተለይም አሁን ከላው ሁኔታ አንጻር፣ ይህ ውይይት ታጋቾችን የማስለቀቅ ጉዳይን ጭምሮ ተጨባጭ እርምጃ የሚፈልጉ ችግሮችን ለመፍታት ጠቃሚ ነው” ብለዋል ምክትል ሚኒስትሩ።

  7. የእስራኤል ጦር ያለፈው ሳምንቱን ጥቃት ከመሩት ውስጥ አንዱን ገደልኩ አለ

    ባለፈው ሳምንት ድንበር ተሻግሮ በእስራኤል ሰፋሪዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት መርቷል የተባለውን የሐማስ አዛዥ አሊ ቃዲን መግደሉን የእስራኤል አየር ኃይል አስታወቀ።

    የእስራኤል የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ሺን ቤት እና የሠራዊቱ ወታደራዊ ደኅንነት ተቋም በሰጡት መረጃ መሠረት ነው የሐማሱ አዛዥ በድሮን ጥቃት የተገደለው ተብሏል።

    አሊ ቃዲ የሐማስ ዋነኛ ኮማንዶ ኃይል “ኑኽባ” የተባለው ቡድን አዛዥ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት በተፈጸመው ድንበር ዘለል ጥቃት ውስጥ ተሳታፊ እንደነበር ተነግሯል።

    የ37 ዓመቱ አሊ አንድ ከእስራኤል የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ጋር ይሠራል የተባለን ሰው ጠልፎ ገድሏል ተብሎ በእስራኤል አስር ቤት ውስጥ ለዓመታት ታስሮ የነበረ መሆኑም ተገልጿል።

    ከእስር ሊወጣ የቻለውም በሐማስ ተይዞ የነበረን የእስራኤል ወታደር፣ ጊላድ ሻሊትን በልውውጥ ለማስለቀቅ በ2011 (እአአ) በተደረሰ ስምምነት መሠረት እስራኤል ከእስር ከፈታቻቸው የቡድኑ አባላት መካከል አንዱ በመሆን ነበር ተብሏል።

  8. ሰበር, ጋዛ ውስጥ አስካሁን ከ2,200 በላይ ሲገደሉ 8,700 ጉዳት ደርሶባቸዋል

    አንድ ሳምንት በሞላው የእስራኤል የአየር ድብደባ ጋዛ ውስጥ አስከ ቅዳሜ እኩለ ቀን ድረስ ቢያንስ 2,215 ሰዎች ሲገደሉ፣ 8,714 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል የፍልስጥኤም ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    በሌላው የፍልስጥኤም ክፍል ዌስት ባንክ ውስጥ ደግሞ 54 ሰዎች ተገድለው፣ 1,100 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ተብሏል።

  9. ሩሲያ በጋዛ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ለፀጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ አቀረበች

    ሩሲያ ጋዛ ውስጥ ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ የሚያስችል የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚጠይቅ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ የፀጥታው ምክር ቤት ባደረገው ዝግ ስብሰባ ወቅት አቀረበች።

    ባለአንድ ገጹ የውሳኔ ሃሳብ አስቸኳይ፣ ዘላቂ እና ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ የሚሆን ተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ ሁሉም ታጋቾች ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲለቀቁ እንዲሁም እርዳታ እንዲቀርብ እና ለመውጣት የሚፈልጉ ሲቪሎች ያለችግር እንዲወጡ የሚጠይቅ ነው።

    በመንግሥታቱ ድርጅት የሩሲያ አምባሳደር የሆኑት ቫዚሊ ኔቤንዚያ ከስብሰባው በኋላ ስለውሳኔ ሃሳቡ ለጋዜጠኞች መግለጫ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    የምክር ቤቱ አባላት በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ተቃውሞ ማንሳት እና ድርድር ማድረግ የሚችሉ ሲሆን፣ ነገር ግን ረቂቁ ወደ መደበኛ ድምጽ አሰጣጥ ይሄድ እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

    አንድ ምዕራባዊ ዲፕሎማት ግን በጉዳዩ ላይ ሩሲያ የምሯን መሆኑን እንደሚጠራጠሩ ተናግረዋል። ጨምረውም ሞስኮ ሃሳቡን ስታዘጋጅ ሌሎች የምክር ቤቱን አባላት ካለማማከሯ በተጨማሪ ሐማስን ሳትጠቅስ አልፋዋለች በማለት ተችተዋል።

    በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የሚወጣ የውሳኔ ሃሳብ ከአባላቱ መካከል ዘጠኝ ድጋፍ የሚያስፍልገው ሲሆን፣ ቋሚ አባላት ከሆኑት ከአሜሪካ፣ ከዩናይትድ ኪንግድም፣ ከፈረንሳይ፣ ከሩሲያ እና ከቻይና ግን ድጋፍ አያስፈለገውም።

    አሜሪካ በፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ውስጥ ወዳጇ የሆነችውን አስራኤልን የሚተች ማንኛውንም ሃሳብ ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣኗን በመጠቀም በተዳጋጋሚ ውድቅ ስታደርግ ቆይታለች።

  10. በእስራኤል የአየር ድብደባ ጋዛ ውስጥ ከ1,300 በላይ ሕንጻዎች ወደሙ

    እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ ለአንድ ሳምንት ባካሄደችው የአየር ድብደባ ከ1,300 በላይ ሕንጻዎች መውደማቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።

    የድርጅቱ የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) እንዳለው በወደሙት ሕንጻዎች ላይ የነበሩ “5,540 ቤቶች” ሲወድሙ 3,750 የሚደርሱ ሌሎች ቤቶች ደግሞ ለመኖሪያ በማይሆኑ ሁኔታ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

  11. በጭንቅ ውስጥ የሚገኙት የሰሜን ጋዛ ነዋሪዎች

    በሰሜን ጋዛ ያሉ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ በእስራኤል የተቀመጠው ገደብ ዛሬ ይጠናቀቃል። የተባበሩት መንግሥታት እንደገመተው አስር ሺዎች ለቀው ወጥተዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በጋዛ ላይ የሚፈጸመው የአየር ድብደባ መጀመሩን በመግለጽ የከፋው ሁኔታ ገና እንሚመጣ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።

    በተጨናነቀ ሁኔታ ሕዝብ በሰፈረበት የሰሜን ጋዛ ያለው ነዋሪ አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ የሚያስጠነቅቅ ጽሁፍ አስራኤል ከበተነች በኋላ ነዋሪው ሽብር ውስጥ ይገኛል።

    በርካቶች መኖሪያቸውን ለቀው ለመውጣት በመኪና እና በእግር በረጅም ሰልፍ ጉዞ ሲጀምሩ፣ በርካቶች ደግሞ ከመኖሪያቸው ላለመውጣት የቆረጡ እንዲሁም ገና እንቅስቃሴ ያልጀመሩ ናቸው።

    የተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎችም ድርጅቶች ይህን ያህል ሕዝብ ከአካባቢው የሚፈናቀል ከሆነ አደጋን እንደሚያስከትል በማስጠንቀቅ፣ እስራኤል በጋዛ ላይ የጣለችውን ከበባ በማንሳት ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ እንድትፈቅድ እየጠየቁ ነው።

    እስራኤል በጋዛ ላይ እየፈጸመች ያለችው የአየር ጥቃት ሐማስን ለማጥፋት ያለመ መሆኑን ስትገልጽ፣ ሐማስ በበኩሉ አስከ መጨረሻዋ የደም ጠብታ እንደሚዋጋ ዝቷል።

    እስራኤል ወደ ጋዛ እግረኛ ሠራዊቷን ለማሰማራት ዝግጅት በማድረግ ቀዳሚ ወታደራዊ እርምጃዎችን እየወሰደች እንደሆነ እየተነገረ ነው።

    ባለፉት ቀናትም ሮኬቶች የሚተኮሱባቸው ስፍራዎችን ኢላማ በማድረግ ወታደሮቿ በተወሰኑ የጋዛ አካባቢዎች ላይ አሰሳ በማካሄድ ስለታገቱ ዜጎቻቸው መረጃዎችን እየሰበሰቡ ነው።

  12. ሐማስ ጥቃት ፈጽሞ እስራኤል ጋዛ ላይ የአየር ድብደባ ከጀመረች አንድ ሳምንት ሆነ

    ልክ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ማለዳ ሐማስ በእስራኤል ላይ በፈጸመው የተቀናጀ ጥቃት የተጀመረው ግጭት ተባብሶ ቀጥሏል።

    ባለፉት ሰባት ቀናት እስራኤል በጋዛ ላይ ቀን አና ሌሊት ያለተቋረጠ የአየር ድብደባ አየፈጸመቸ ሲሆን፣ ሐማስም ወደ እስራኤል ሮኬቶቸን ሲተኩሰ ቆይቷል።

    በዚህም ባለፉት ቀናት ከሦስት ሺህ በላይ ሰዎች ከሁለቱም ወገን ሲገደሉ፣ ከፍልስጥኤም በኩል ከ300 ሺህ በላይ ለመፈናቀል መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።

    ባለፈው አንድ ሳምንት የተከሰቱ ዋና ዋና ነገሮች ምንድን ናቸው።

    • የሐማስ ታጣቂዎቸ የዛሬ ሳምንት በአስራኤል ላይ ጥቃት ፈጽመው 1,300 ሰዎችን ሲገድሉ፣ 150 ሰዎችን ደግሞ አግተው ወደ ጋዛ ወስደዋል።
    • እስራኤል ላለፉት ቀናት በጋዛ ላይ በወሰደችው የአጸፋ የአየር ድብደባ 1,900 ያህል ሰዎች መገደላቸወን የአካባቢው ባለሥልጣናት አስውቀዋል።
    • ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ፍልስጥኤማውያን የእስራኤል ሠራዊት የምድር ላይ ጥቃት ከመክፈቱ በፊት አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ታዘዋል።
    • በሰሜናዊ ጋዛ ያሉ ነዋሪዎች እስእራኤል አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ የ24 ሰዓት የጊዜ ገደብ ካስቀመጠች በኋላ በመኪና፣ በጋሪ እና በእግር ከቀያቸው እየሸሹ ነው።
    • የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእስራኤልን ውሳኔ አሰቃቂ ያለው ሲሆን፣ አሜሪካ ደግሞ አስራኤል ሰላማዊ ሰዎች እንዳይገደሉ ጥንቃቄ እድታደርግ ጠይቃለች።
    • የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንክን ጋዛ ውስጥ “ከጥቃት የተከለለ አካባቢ” እንዲለይ ከእስራኤል ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
    • እስራኤል ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሚኖርባት የሐማስ መቀመጫ በሆነችው ጋዛ ላይ ከምትፈጽመው የአየር ጥቃት በተጨማሪ ወደ ግዛቱ ምንም አይነት ነገር እንዳይገባ እና እንዳይወጣ አግዳለች። በዚህም ምክንያት ጋዛ ውስጥ ያለው ነዳጅ፣ ምግብ እና ውሃ እየተሟጠጠ ነው።
  13. ዌስት ባንክ ውስጥ በተካሄደ ተቃውሞ ወቅት 11 ሰዎች ተገደሉ

    የፍልስጥኤም የጤና ሚኒስቴር ዌስት ባንክ ውስጥ በተቃዋሚዎች እና በእስራኤል ወታደሮች መካከል በተከሰተ ግጭት 11 ሰዎች መገደላቸውን አስታወቀ።

    ዛሬ አርብ ከጋዛ ርቆ በሚገኘው የፍልስጥኤም ግዛት በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ጋዛ ውስጥ ወገኖቻቸው ከቤታቸው እንዲፈናቀሉ መገደዳቸውን በመቃወም ነው አደባባይ ወጥተው ተቃውሞ ያሰሙት።

    ሰዎቹ የተገደሉት ዌስት ባንክ ውስጥ በሚገኙት ራማላህ፣ ናብሉስ፣ ሄብሮን እና ቱልካራም ውስጥ በተካሄዱ ተቃውሞዎች ወቅት ከእስራኤል ወታደሮች ጋር በመጋጨታቸው ነው።

    ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪም ከአንድ መቶ የሚበልጡ ሌሎች ደግሞ የመቁሰል ጉዳት እደደረሰባቸው ተዘግቧል።

    በዌስት ባንክ እና በምሥራቅ ኢየሩሳሌም ውስጥ የሚገኙ ፍልስጥኤማውያን ከ1967 (እአአ) ጀምሮ በእስራኤል ወረራ ስር ነው የሚኖሩት።

  14. በትንሽ ቦታ ብዙ ሕዝብ ተጨናንቆ የሚኖርባት ጋዛ

    ጋዛ ሰርጥ በዓለም ላይ ብዙ ሕዝብ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠጋግቶ ከሚኖርባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። በዚህም 365 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሆን ስፋት ባለው ግዛቷ ውስጥ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይኖራል።

    በእያንዳንዷ የጋዛ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ላይ 5,700 ሰዎች ተጠጋግተው ይኖራሉ። ይህ የለንደን ሕዝብ ካለው የጥግግት መጠን ጋር ተመሳሳይ ነው።

    ከላይ የተቀመጠው ካርታ እንደሚያሳየው ደግሞ ከዋዲ ጋዛ በስተሰሜን ባለው የጋዛ ከተማ ውስጥ ከ9,000 ሰዎች በላይ በእያንዳንዱ ስኩዌር ኪሎ ሜትሮች ላይ ሰፍረው ይገኛሉ።

  15. ሐማስ በእስራኤል ላይ የሚፈጽመው የሮኬት ጥቃት መቀጠሉን አስታወቀ

    ዛሬ አርብ ሰባተኛ ቀኑን በደፈነው ግጭት ፍልስጥኤማዊው ታጣቂ ቡድን ሐማስ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን መተኮሱን ቀጥሏል።

    ቡድኑ እንዳለው ዛሬ አርብ ከሰዓት በኋላ በሰሜናዊ እስራኤል ውስጥ ወደምትገኘው ሳፊድ ከተማ ሚሳኤል አስወንጭፏል።

    የእስራኤል የጦር ኃይሎች ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ በኤክስ (ትዊተር) ላይ እንዳሰፈሩት ከጋዛ ወደ ሰሜናዊ እስራኤል ክልል የተተኮሱ ሮኬቶች እንዲከሽፉ ተደርገዋል ያሉ ሲሆን፣ ነገር ግን የተተኮሰባትን ከተማ ስም አልጠቀሱም።

    ሐማስ ወደ ባሕር ዳርቻ ከተማዋ ቴል አቪቭ ሮኬቶችን ካስወነጨፈ በኋላ በከተማዋ ውስጥ የአየር ጥቃት መስጠንቀቂያ ደወል ድምጽ ተሰምቷል።

    ታጣቂው ቡድን ባለፈው ቅዳሜ በፈጸመው ጥቃት 1,300 ሰዎችን ወደ ገደለባቸው የደቡብ እስራኤል ከተሞች ወደሆኑት አሽኬሎን፣ ስዴሮት እና ቤሪ ሮኬቶችን መተኮሱን ገልጿል።

    እስራኤል በጋዛ ላይ የአጸፋ ጥቃት እየፈጸመችበት ባለበት በአሁኑ ጊዜ ሐማስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ሲቪሎች ወደ ሚኖሩባቸው የእስራኤል አካባቢዎች ተኩሷል።

  16. የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ሐማስን በመደገፍ እንሚሰለፍ ገለጸ

    የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ከእስራኤል ጋር ግጭት ውስጥ የገባው ፍልስጥኤማዊውን ሐማስን በመደገፍ እንደሚሰለፍ አስታወቀ።

    የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህ ሊባኖስን በመጎብኘት ላይ ካሉት የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆሴይን አብዶላሃይን ጋር ተገናኝተው በተወያዩበት ጊዜ፣ ጋዛ ውስጥ የሚፈጸመውን “የጦር ወንጀል ለመቋቋም ያለጥርጥር የጋራ ምላሽን መነሳቱ አይቀርም” ሲሉ ተናግረዋል።

    በተመሳሳይ የሄዝቦላህ ምክትል መሪ ሐማስ ከእስራኤል ጋር በሚያደርገው ጦርነት ውስጥ “ጊዜው ሲደርስ” ቡድናቸው ለመሳተፍ “ሙሉ ለሙሉ ዝግጁ ነው” ሲሉ በቤይሩት ዳርቻ በተደረገ ሰልፍ ላይ ተናግረዋል።

    ሄዝቦላህ የፍልስጥኤም አጋሩን ሐማስን ለመደገፍ ወስኖ በጦርነቱ ከተሳተፈ እና እስራኤል ላይ ጥቃት ከከፈተ፣ አዲስ የጦርነት ግንባር ሊከፈት ይችላል የሚል ተጨባጭ ስጋት አለ።

    እንደ ፍልስጥኤሙ ሐማስ ሁሉ የሊባኖሱ ሄዝቦላህ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በአሜሪካ እና በሌሎች ምዕራባውያን አገራት ሽብርተኛ ድርጅት ተብሎ ተፈርጇል።

    ሄዝቦላህ በሊባኖስ ውስጥ በፖለቲካ እና በወታደራዊ መስክ ኃያል ሚና ያለው ሲሆን፣ የምዕራባውያን ባላንጣ ከሆነችው ኢራን ጋር ወዳጅ ነው።

  17. የእስራኤልን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ ነዋሪዎች ከሰሜናዊ ጋዛ እየሸሹ ነው

    የእስራኤልን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ በሰሜናዊ ጋዛ የሚገኙ በርካታ ነዋሪዎች ባገኙት የመጓጓዣ ዘዴ በመጠቀም አካባቢውን ለቀው እየወጡ ይገኛሉ።

    የእስራኤል ሠራዊት ከጋዛ ነዋሪ ግማሹ ከሚገኝበት አካባቢ ሕዝቡ ለቆ እንዲወጣ ያዘዘው በጋዛ ውስጥ ላሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ነው።

    ሰሜናዊ ጋዛ 1.1 ሚሊዮን ነዋሪዎች በ24 ሰዓታት ውስጥ አካባቢውን ለቀው ወደ ደቡብ እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ከተሰጠ በኋላ ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ ፍልስጥኤማውያን መኖሪያቸውን እየለቀቁ በመውጣት ላይ ናቸው።

    እጅግ በተጨናነቀ ሁኔታ ከሚኖርባቸው የዓለማችን ክፍሎች መካከል አንዷ በሆነችው ጋዛ ውስጥ ካለው ነዋሪ ግማሽ የመሆኑት ከ18 ዓመት በታች ያሉ ናቸው።

  18. ሰበር, ሐማስ በጋዛ 13 ታጋቾች በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደላቸውን ገለጸ

    ሐማስ በእገታ ከወሰዳቸው ውስጥ ቢያንስ 13 እስራኤላውያንን እና የውጭ አገራት ዜጎች እስራኤል በጋዛ ሰርጥ እያደረገችው ባለችው የአየር ጥቃቶች መገደላቸው አስታወቀ።

    ታጋቾቹ ባለፉት 24 ሰዓታት እስራኤል በምታደርገው የአየር ጥቃቶች መገዳላቸውንም ነው የሃማስ የጦር ክንፍ የገለጸው።

    "13 እስረኞች፣ የውጭ ዜጎችን ጨምሮ" የእስራኤል ተዋጊ ጄቶች ኢላማ ባደረጓቸው አምስት ስፍራዎች መገደላቸውን የኢዜዲን አል ቃሳብ ብርጌድ በመግለጫው አስፍሯል።

    ሐማስ ከቀናት በፊት በሰነዘረው ድንገተኛ ጥቃት ወደ 150 የሚጠጉ ታጋቾችን ወስዷል። እስራኤል ያለምንም ማስጠንቀቂያ የሰላማዊ ዜጎችን መኖሪያ ቤቶችን በቦምብ የምትደበድብ ከሆነ ታጋቾችን ለመግደልም ዝቷል።

    ታጋቾች ተገድለዋል መባሉን ተከትሎ የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስትር ግራንት ሻፕስ መረጃውን በጥንቃቄ እንደሚያዩት ቢገልጹም ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረባቸው አይቲቪ ለተሰኘው ሚዲያ ተናግረዋል።

  19. ብሊንከን እና የፍልስጥኤሙ ፕሬዚዳንት በዮርዳኖስ ተገናኙ

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ከፍልስጥኤሙ ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ ጋር ተገናኙ።

    ብሊንከን እና ፕሬዚዳንቱ የተገናኙት ዛሬ ጥቅምት 2/2016 ዓ.ም በዮርዳኖስ ነው።

    ዌስት ባንክን የሚመራው የማህሙድ አባሱ ፋታህ እና የጋዛ ሰርጥን የሚቆጣጠረው ታጣቂው ቡድን ሐማስ ተቀናቃኝ ናቸው።

    ብሊንከን ከዮርዳኖሱ ንጉስ አብዱላህ ጋር በአማን ይገናኛሉ ተብሏል።

    የውጭ ጉዳይ ኃላፊው ትናንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ተገናኝተው የነበረ ሲሆን በሐማስ ተገደሉ የተባሉ የሞቱ ህጻናትን ምስሎችም እንዲያዩ መደረጋቸውም ተገልጿል።

  20. በጠና የታመሙ ፍልስጥኤማውያንን ከሰሜን ጋዛ ማስወጣት “የሞት ፍርድ ነው”_ የዓለም ጤና ድርጅት

    እስራኤል 1.1 ሚሊዮን ፍልስጥኤማያውን ከሰሜን ዋዲ ጋዛ ወጥተው ወደ ደቡባዊ ጋዛ እንዲሸሹ ትዕዛዝ መስጠቷን ተከትሎ በጠና የታመሙ ነዋሪዎችን ማስወጣት “የሞት ፍርድ ነው” ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

    የዓለም ጤና ድርጅት በሆስፒታል ውስጥ ያሉ ህመምተኞችን በጭራሽ ማስወጣት እንደማይቻልም ነው የገለጸው።

    "በጠና የታመሙ እና የመዳን እድላቸው በድጋፍ ሰጪ ቬንትሌተሮች ብቻ የሆኑ በርካታ ፍልስጥኤማውያን በሆስፒታሎች አሉ" ሲሉም የዓለም ጤና ድርጅት ቃለ አቀባይ ታሪክ ጃሳሬቪች ተናግረዋል።

    "እነዚህን ህመምተኞች ማንቀሳቀስ ማለት የሞት ፍርድ ነው። የጤና ባለሙያዎች ይህንን ያድርጉ ማለት ከጭካኔ በላይ ነው" ሲሉም አስረድተዋል።