በኢትዮጵያ በየዕለቱ በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚያገግሙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

በኢትዮጵያ ተጨማሪ 206 ሰዎች ላይ የኮሮናቫይረስ ሲገኝ 250 ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸው ሲነገር የአንድ ሰው ህይወት ደግሞ አልፏል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ዛሬ ባወጡት ዕለታዊ የወረርሽኙ ሁኔታ መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት ባለፉት 24 ሰዓታት በአገሪቱ በ3 ሺህ 922 ሰዎች ላይ ምርመራ ተደርጎ 206ቱ ላይ የኮሮናቫይረስ ተገኝቷል።
በተጨማሪም ቀደም ሲል በወረርሽኙ መያዛቸው ተረጋግጦ የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው ከነበሩ ሰዎች መካከል ደግሞ ተጨማሪ 250 ሰዎች ከበሽታው በማገገማቸው በአገሪቱ ከወረርሽኙ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 4550 ሆኗል።
ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘም የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን ዕለታዊው መግለጫ ያመለከተ ሲሆን ውጤቱ የተገኘው በአስከሬን ላይ በተደረገ ምርመራ ላይ ሲሆን በዚህም እስካሁን ድረስ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 128 ደርሷል።
በኢትዮጵያ እስካሁን 289 ሺህ 550 ሰዎች ላይ ምርመራ የተደረገ ሲሆን ከእነዚህ መካከልም በአጠቃላይ 7 ሺህ 766 ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች ተገኝተዋል።


















