በምዕራብ አፍሪካ አገራት ውስጥ ወረርሽኙ እየተስፋፋ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በበርካታ አፍሪካ አገራት ውስጥ በፍጥነት እየተስፋፋ ይገኛል። በምዕራብ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ በርካታ አገራት ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን በሚያወጧቸው ሪፖርቶች እያመለከቱ ነው። ከእነዚህም መካከል፡
• ኮትዲቯር፡ አዲስ በበሽታው የተያዙ 402 ሰዎችን በማግኘት አጠቃላይ የህሙማኑ ቁጥር 7,276 ደርሷል። ከእነዚህ ውስጥም ሦሰት ተጨማሪ ሰዎች መሞታቸው በመመዝገቡ አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር 52 ሆኗል።
• ሴኔጋል፡ 144 አዳዲስ ህሙማን ማግኘቷን ስታስታውቅ ተጨማሪ ሦስት ሰዎች ሞተዋል። አጠቃላይ የህሙማን ቁጥር 5,783 የደረሰ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ደግሞ 55 ደርሷል።
• ኒጀር፡ ቅዳሜ ከሌላ አገር በመጡ ዘጠኝ ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል። በአጠቃላይ ኒጀር ውስጥ 1,035 በሽታው ያለባቸው ሰዎች ተመዝግበው 67ቱ ህይወታቸው አልፏል።
• ቶጎ፡ አዲስ ስድስት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ያገኘች ሲሆን በአጠቃላይ 561 ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱን አስታውቃ የ13 ሰዎች ሞት ተመዝግቧል።
• ቤኒን፡ ውስጥ 53 አዳዲስ ህሙማን በመመዝገባቸው በአገሪቱ ያሉትን የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር ወደ 650 ከፍ አድርጎታል። እስካሁንም የ11 ሰዎች ህይወት አልፏል።
• ቡርኪናፋሶ፡ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በማኅበረሰብ ደረጃ እየተሰራጨ መሆኑን መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው። በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 902 የደረሰ ሲሆን 53 ሰዎች ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ምክንያት ህልፈት ተዳርገዋል።














