በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከሁለት ሺህ ሲሻገር ሰባት ሰዎች ሞቱ
በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሬ እያሳየ ባለባት ኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት 86 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ የህሙማኑን ቁጥር 2 ሺህ 20 አድርሶታል። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በኤካ ሆስፒታል ውስጥ በህክምና ላይ እያለች በሰላም የተገላገለችው እናትን ጨምሮ የሰባት ሰዎች ህይወት አልፏል።በአጠቃላይም ሃገሪቷ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎች ቁጥር 27 መድረሱን የጤና ሚኒስትርና የህብረተሰብ ጤና ተቋም በጋራ የሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ ጠቁሟል። ኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሁሌም ቢሆን ከንክኪ በኋላ እጅን በሳሙና በሚገባ መታጠብ፣ በሚገኙበት ስፍራ ሁሉ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ የእርስዎንም የሌሎችን ጤና ይጠብቃል።
የቀጥታ ሽፋን
"ቫይረሱ በምጣኔ ሐብት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ለ10 ዓመታት ይዘልቃል" የዓለም ባንክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ዴቪድ ማልፓስ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ምጣኔ ሐብት ላይ ያደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት በመግለጽ የምጣኔ ሐብት ድቀቱ ለአስር ዓመታት ሊዘልቅ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚደንቱ ባለፈው የጎርጎሳውያኑ ወር በኮቪድ-19 ወረርሽን ምክንያት 60 ሚሊየን ሰዎች ለከፋ ድህነት ሊጋለጡ እንደሚችሉና አማካይ የነፍስ ወከፍ የቀን ገቢም ከ1.90 ዶላር በታች እንደሚሆን አስጠንቅቀው ነበር፡፡
ሆኖም ባሳለፍነው አርብ በሰጡት ቃለ ምልልስ አማካይ የአንድ ሰው የቀን ገቢ ከአንድ ዶላር ያነሰ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል፡፡
ዴቪድ ማልፓስ "በወረርሽኙ ሳቢያ ገቢ ከማጣት ባሻገር የጤናና ማህበራዊ ቀውሱ ከባድ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ራዲዮ 4 ተናግረዋል፡፡
"በአሜሪካ ያለውን የአክሲዎን ዋጋ ስናየው በአንጻራዊነት ከፍተኛ ነው፡፡ ነገር ግን በደሃ አገራት የሚኖሩ ሰዎች ሥራ ማጣት ብቻ ሳይሆን መደበኛ ባልሆኑ ዘርፎች እንኳን ምንም ዓይነት ሥራ ማግኘት አልቻሉም፤ ይህም ለ10 ዓመታት ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡" ሲሉ አክለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከሁለት ሺህ ሲሻገር ሰባት ሰዎች ሞቱ

በኢትዮጵያ በባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገ 6 ሺህ 92 የላብራቶሪ ምርመራ 86 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸዋል።
በዚህም መሰረት በሃገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 2 ሺህ 20 አድርሶታል።
ከዚህም በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በኤካ ሆስፒታል ውስጥ በህክምና ላይ እያለች በሰላም የተገላገለችው እናትን ጨምሮ የሰባት ሰዎች ህይወት አልፏል።
በአጠቃላይ ሃገሪቷ በቫይረሱ ያጣቻቸው ዜጎች ቁጥር 27 መድረሱን የጤና ሚኒስትርና የህብረተሰብ ጤና ተቋም በጋራ የሚያወጡት ዕለታዊ መግለጫ ጠቁሟል።
በዛሬው እለት በቫይረሱ ከተያዙት መካከል 66 ከአዲስ አበባ፣ ሰባት ከኦሮሚያ፣ ሰባት ከትግራይ፣ አራት ከደቡብ ክልል፣ አንድ ሰው ደግሞ ከድሬዳዋ አስተዳደር ናቸው።
በትናንትናው ዕለት 63 ሰዎች ከበሽታው ማገገማቸውም ተገልጿል፡፡
ሃገሪቷ በአጠቃላይ ያከናወነችው የላብራቶሪ ምርመራ ቁጥር 142 ሺህ 960 ደርሷል።

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Public Health Institute

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Public Health Institute
"ቻይና የክትባቱ ምርምር እንዳይሳካ ለማደናቀፍ እየሞከረች እንደሆነ ማስረጃ አለን" የአሜሪካ ሴናተር

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ ሪፐብሊካን ሴናተር ሪክ ስኮት ቻይና የኮሮናቫይረስ ክትባት እንዳይሳካ የማደናቀፍ ሙከራ እያደረገች ነው ሲሉ ወነጀሉ፡፡
ሴናተሩ "ቻይና ባላንጣ ለመሆን ወስናለች" ሲሉ ለቢቢሲ አንድሪው ማር ፕሮግራም ተናግረዋል፡፡
"ይህንን ክትባት ማግኘት አለብን፤ ነገር ግን በሚገርም ሁኔታ ቻይና ሆነ ብላ እኛን ለማደናቀፍ ወይም ሂደቱን ዘገምተኛ ለማድረግ እየሞከረች እንደሆነ ማስረጃ አለን" ብለዋል ሴናተር ሪክ ስኮት፡፡
ሴናተሩ አክለውም "ክትባቱን እኛ ወይም እንግሊዝ አሊያም በሌሎች የአውሮፓ አገራት ቀድሞ ከተገኘ ሁላችንም እንካፈለዋለን፤ ቻይና ግን የዚህ ተጠቃሚ አትሆንም" ብለዋል፡፡
በቻይና ላይ ውንጀላውን ለመሰንዘር ያላቸው ማስረጃ ምን እንደሆነ የተጠየቁት ሴናተሩ፤ "ማስረጃ አለን፤ ማስረጃው የመጣውም ከደህንነት ኤጀንሲ ነው፤ ቻይና ክትባቱን ለማደናቀፍ አሊያም ሂደቱ እንዳይፋጠን ለማድረግ ሆነ ብላ እየሰራች እንደሆነ ማስረጃ አለ፡፡" ሲሉ መልሰዋል፡፡
"ቻይና በሁላችንም ላይ ያደረገችው ተስፋ አስቆራጭ ቢሆንም እነርሱ ግን ይህንንም ክደዋል፤ በመሆኑም በተሻለ ሁኔታ መዘጋጀት አለብን" ሲሉ ሴናተሩ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ቻይና በበኩሏ ኮሮናቫይረስ በስፋት ሳይታወቅና ሳይዛመት በፊት በጎርጎሳውያኑ ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ስለሁኔታው ለአሜሪካ አስረድቻለሁ ብላለች፡፡
ፕሬዚደንት ዢ ጂንፒንግም የቫይረሱን ክትባት ቻይና ካገኘች ለዓለም እንደምታሰራጭ ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚደንቱ አክለውም በማደግ ላይ ባሉ አገራትም የክትባት ተደራሽነትና ክትባቱ አቅምን ያገናዘበ መሆኑን ማረጋገጥ የቻይና ድርሻ ይሆናል ብለዋል፡፡
በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ400 ሺህ ተሻገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአለማችን ላይ በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ ባለው ኮሮናቫይረስ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 400 ሺህ ተሻግሮ፣ 400 ሺህ አስራ ሶስት መድረሱን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ አሳውቋል።
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም 6.9 ሚሊዮን መድረሱንና ከነዚህም ውስጥ 3.4 ሚሊዮን የሚሆኑት ማገገማቸውን ከዩኒቨርስቲው የተገኘው መረጃ አመላክቷል።
በታህሳስ ወር በቻይናዋ ውሃን ግዛት እንደተነሳ በሚታመነው በዚህ ቫይረስም 183 ሺህ 760 አፍሪካውያን የተያዙ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ 81 ሺህ 498 ሰዎች አገግመዋል።
ከሌሎች አህጉራት ጋር ሲነፃፀር በአፍሪካ ውስጥ የተመዘገበው የሟች ቁጥር አነስተኛ የሚባል ሲሆን፤ እስካሁንም 5 ሺህ ስልሳ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።
በሩሲያ በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

በሩሲያ ባለፉት 24 ሰዓታት 8ሺህ 984 ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ይህም አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 467 ሺህ 673 አድርሶታል፡፡
እንደ አገሪቷ መረጃ ከሆነ በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም በ134 ጨምሮ እስካሁን በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 5 ሺህ 859 ሆኗል፡፡
ሩሲያ ልክ እንደ ሌሎች አብዛኞቹ አገራት ሁሉ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ለሳምንታት የጣለችውን ቤት የመቀመጥ ገደብ ተከትሎ የምጣኔ ሐብት ቀውስ እያጋጠማት ነው፡፡
በዚህም ምክንያት የፕሬዚደንት ፑቲን የሕዝብ ተቀባይነት በ20 ዓመታት ውስጥ ወደ ዝቅተኛ ደረጃ ወርዷል፡፡
የተቃውሞ ሰልፎች የወረርሽኙን መዛመት እንዳይጨምሩ ስጋት መኖሩ ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ እጁ ከኋላ እንደተጠፈረ ከመሬት ላይ ተጣብቆ ነጭ ፖሊስ አንገቱን በጉልበቱ ለዘጠኝ ደቂቃ ተጭኖት ህይወቱ ማለፉን ተከትሎ የተነሳው ተቃውሞ ከአሜሪካ አልፎ በተለያዩ የአለማችን አገራት ያሉ ፀረ-ዘረኝነት ተቃውሞዎችን አቀጣጥሏል።
ከሰሞኑም በዩኬ የ'ብላክ ላይቭስ ማተር' እንቅስቃሴን በሚደግፉ የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ሊጨምር እንደሚችል የእንግሊዙ ጤና ሚኒስትር ፀሐፊ ማት ሃንኮክ አስጠንቅቀዋል።
ሚኒስትሩ ከስካይ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ምንም እንኳን ለእኩልነት የሚደረጉ ትግሎችን ቢደግፉም "የኮሮናቫይረስ ስጋት ከፍተኛ በሆነበት በአሁኑ ወቅት በርካታ ሰዎች ሆኖ መሰብሰብ ከመመሪያ ውጭ ነው። ምክንያቱም የወረርሽኙን የመዛመት ሁኔታ ይጨምራል" ብለዋል።
አክለውም "እባካችሁ ከስድስት ሰዎች በላይ ሆናችሁ አትሰባሰቡ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እያከናወነው ያለውንም ሥራ ያሰናክለዋል" በማለት ተማፅነዋል።
ፈረንሳይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ያለአግባብ በሚጥሉት ላይ ቅጣት ልትጨምር ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በፈረንሳይ ጎዳናዎችና በሌሎች ሥፍራዎች ያገለገሉ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛዎች (ማስኮች) ያለአግባብ ተጥለው እየታዩ ነው፡፡
ይህንንም ተከትሎ የፈረንሳይ መንግሥት የተጠቀሙበትን ማስክ ያለአግባብ የሚጥሉ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ቅጣት ለመጣል ወስኗል፡፡
አገሪቷ ከዚህ በፊትም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) አሊያም የሲጋራ ቁራጮችን የሚጥሉ ሰዎች 68 ዩሮ (2ሺህ 600 ብር) እንዲቀጡ የሚያዝ ሕግ ያላት ሲሆን፤ አሁን ግን ይህንን ቅጣት ወደ 135 ዩሮ (5ሺህ 200 ብር) ከፍ አድርጋለች፡፡
ቅጣቱ የእጅ ጓንቶችንና ሌሎች ቆሻሻዎችን የሚጥሉትንም ይጨምራል፡፡
የአካባቢ ሚኒስትር ብሩን ፖይርሰን ለኤኤፍ ፒ ዜና ወኪል "ማንኛውም ሰው ያለ አግባብ መሬት ላይ የሚጣሉ ቆሻሻዎች መዳረሻቸው ውቅያኖስ መሆኑን መገንዘብ አለበት" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አፍሪካ ለኮሮናቫይረስ መድሃኒት እንዳታገኝ የተወጠነ ሴራ አለ?
የጣሊያን መንግሥት ለወረርሽኙ የሰጠውን ምላሽ ተቃውሞ ወደ አመጽ ተለወጠ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የጣሊያን መንግሥት ኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር የሰጠውን ምላሽ ለመቃወም አደባባይ የወጡ ፅንፈኛ የሚባሉት የ'ፋር ራይት' አክራሪዎችና ቀንደኛ የእግር ኳስ ደጋፊዎች መጋጨታቸው ተገለጸ፡፡
በዋና መዲናዋ ሮም ከተማ የተቀሰቀሰው አመጽ የጀመረው በሰልፈኞቹ መካከል ግጭት ከተፈጠረ በኋላ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
አንዳንድ ሰልፈኞች ጠርሙሶችን፣ ድንጋይ እና የጭስ ቦምብ ወደ ፖሊስ፣ ጋዜጠኞችና ፎቶ አንሽዎች በመወርወር 'ጋዜጠኞች አሸባሪዎች' እያሉ ሲጮሁ እንደነበር አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
ፖሊስም ግጭቱን ለማብረድ ውሃና አስለቃሽ ጭስ የተጠቀመ ሲሆን በርካታ ሰዎችንም አስሯል፡፡
በመቶዎች የሚቆጠሩት እነዚህ ተቃዋሚዎች አደባባይ የወጡት መንግሥት ለወረርሽኙ የሰጠውን ምላሽና ይህንንም ተከትሎ በተከሰተው የምጣኔ ሐብትና የሥራ እድል ቀውስ ምክንያት ሥልጣኑን እንዲለቅ ለመጠየቅ ነው፡፡
በጣሊያን ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ከ234 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ከ33ሺህ 800 በላይ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሕይወታቸው አልፏል፡፡
ጣሊያን ከዓለም አገራት በቫይረሱ ክፉኛ የተጠቃች አገር ናት፡፡
አገሪቷ አሁን ላይ የጣለቻቸውን ገደቦች ለማላላት የመጨረሻውን ደረጃ የጀመረች ሲሆን ይህም የአገር ውስጥ ጉዞዎችን ለመፍቀድና ዓለም አቀፍ ድንበሮቿንም ለመክፈት አስችሏታል፡፡
ሱቆች፣ ካፍቴሪያዎች፣ ምግብ ቤቶች በድጋሜ በሮቻቸውን ለተጠቃሚዎች ክፍት አድርገዋል፡፡ በቅርቡም የቱሪስት መዳረሻዎች ጎብኝዎችን መቀበል ጀምረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስተር ጉሴፔ ኮንቴ መንግሥት ማህበራዊ ክፍያን ለማፋጠንና ወሳኝ የግብር ማሻሻያ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ብራዚል የኮቪድ-19 መረጃዎቿን ከድረ ገጿ ለምን አጠፋች?
እንደምን አደራችሁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጭማሬ እያሳየ ባለባት ኢትዮጵያ በትናንትናው ዕለት 129 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ የህሙማኑን ቁጥር 1 ሺህ 934 አድርሶታል። ከነዚህም ውስጥ 281 አገግመዋል።
ከሰሞኑ በፅኑ ህመም ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ከአስር በታች ነበር። በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች መጨመር ተከትሎ የፅኑ ህሙማንም ቁጥር መጨመር አሳይቷል፤ በትናንትናው ዕለትም 27 ፅኑ ህሙማን በክትትል እንደሚገኙም ተገልጿል።
በትናንትናውም ዕለት የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ የ80 አመት ሴት ለሌላ ህክምና ወደ ሆስፒታል መጥተው ህይወታቸው ወዲያውኑ በማለፉ በተደረገላቸው ምርመራ የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸዋል።
ሃገሪቷ በቫይረሱ ያጣቻቸውን ሰዎች ቁጥር 20 አድርሶታል። ሃገሪቱ የመመርመር አቅሟንም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረች ሲሆን እስካሁንም የተከናወኑ የላብራቶሪ ምርመራዎች ወደ 137ሺህ ደርሷል።
የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሁሌም ቢሆን ከንክኪ በኋላ እጅን በሳሙና በሚገባ መታጠብ፣ በሚገኙበት ስፍራ ሁሉ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ የእርስዎንም የሌሎችን ጤና ይጠብቃል። ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በቀጥታ ዘገባችን እዚህ ታገኛላችሁ።
ቢሊየነሩ ቢል ጌትስን ለሴራ ትንተና ያጋለጣቸው ምንድን ነው?
“ቫይረሱ በኢራን ዘለግ ላለ ጊዜ ሊቆይ ይችላል”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢራን ፕሬዘዳንት ሀሰን ሮሐኒ፤ ኮሮናቫይረስ ዘለግ ላለ ጊዜ በአገሪቱ ሊቆይ እንደሚችል ዜጎችን አስጠንቅቀዋል።
ኢራን ከሚያዝያ ወዲህ እንቅስቃሴ ላይ ጥላ የነበረውን ገደብ እያላላች ነው። ባለፉት ጥቂት ቀናት በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እንደ አዲስ እየጨመረ መጥቷል።
ማክሰኞ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 3,574 ሲሆን፤ ይህም ከመጋቢት ወዲህ ከፍተኛው ቁጥር ነው።
ሮሐኒ፤ “በሽታው በ15 ቀን ወይም በወር ይጠፋል ብላችሁ እንዳታስቡ” ብለው አስጠንቅቀዋል።
በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ የመጣው ሠርግ በመበራከቱ መሆኑም ፕሬዘዳንቱ ተናግረው፤ ሰዎች እንዳይሰባሰቡ መክረዋል።
የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት እንዳይላሽቅ ሲባል ንግድ እንዲጀመር ከመፍቀድ ውጪ አማራጭ እንደሌለ ሮሐኒ ተናግረዋል።
በኢራን በበሽታው የተያዙ ሰዎች 167,156 ሲሆኑ 8,134 ሰዎች እንደሞቱ የጆንስ ሆፕኪንስ መረጃ ይጠቁማል።
አውስትራሊያውያን 'የጥቁር ሕይወት ዋጋ አላት' እንቅስቃሴን ተቀላቀሉ
ሰበር, በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች 20 ሲደርስ ተጨማሪ 129 ሰዎች ቫይረሱ ተገኘባቸው

በባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በኢትዮጵያ በተደረገው 5500 የላብራቶሪ ምርመራ 129 ተጨማሪ ሰዎች ኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸዋል።
ሪፖርቱ ጨምሮም 19 ተጨማሪ ሰዎች ከቫይረሱ ማገገማቸው ያመለከተ ሲሆን በወረርሽኙ ሰበብ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 20 መድረሱም ተነግሯል።
ከዚህ በተጨማሪም ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ አንድ የ80 ዓመት ሴት የአዲስ አበባ ነዋሪ ሕይወት አልፏል።
ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች 75 ወንዶች እና 54 ሴቶች መሆናቸውንም መግለጫው አመላክቷል። የዕድሜ ክልላቸውም ከ1 እስከ 90 መሆኑ ተገልጿል።
ከ129ኙ ግሰለቦች መካከል 124 ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ የተቀሩት የደቡብ አፍሪካ፣ የአሜሪካ፣ የኤርትራ፣ የተባበሩት አረብ አሜሬትስና የሱዳን ዜጎች ናቸው።
101 ግለሰቦች ከአዲስ አበባ፣ 10 ሰዎች ከአማራ ክልል፣ 6 ከሶማሊ ክልል፣ ከትግራይና ከኦሮሚያ ክልሎች እያንዳንዳቸው 5 ሰዎች፤ እንዲሁም አንድ ሰው ከጋምቤላ ሌላ አንድ ሰው ደግሞ ከሐረሪ መሆኑ ተነግሯል።
በአጠቃላይ በአገሪቱ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች 1934 የደረሰ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 281 ሰዎቹ አገግመዋል።
ኢትዮጵያ እስከዛሬ [ቅዳሜ] ሪፖርት ድረስ 136 ሺህ 868 ሰዎችን መርምራለች።
ሕንድ ከጣልያን በላይ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን መዘገበች

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES
በሕንድ ባለፉት 24 ሰዓታት 10 ሺህ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጧል። በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ጣልያን ውስጥ ከተመዘገበው በላይ ሆኗል።
ሕንድ በወረርሽኙ በተያዙ ሰዎች ቁጥር ከዓለም ስድስተኛ ናት። በአጠቃላይ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 236,657 ሲሆን 6,649 ሰዎች ሞተዋል።
የሙምባይ የጤና ተቋማት ከአቅማቸው በላይ በህሙማን ተጨናንቀዋል። በደልሂም ሆስፒታሎች ከሚችሉት በላይ ህሙማን እንደተቀበሉ ተገልጿል።
በሌላ በኩል መደብሮች፣ የእምነት ተቋሞች፣ ሬስቶራንቶችና ቢሮዎች ከሰኞ ጀምሮ ይከፈታሉ ተብሏል።
ከጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ በተገኘው መረጃ መሠረት ሕንድ በበሽታው በተያዙ ሰዎች ብዛት ከዓለም ስድስተኛ ብትሆንም በሟቾች ቁጥር 12ኛ አገር ናት።
እጅን በቀን ቢያንስ አስር ጊዜ መታጠብ ኮሮናን ለመከላከል አንዱ መንገድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቀን ውስጥ ቢያንስ 10 ጊዜ እጅን በሳሙና መታጠብ እንደ ኮሮናቫይረስ አይነት ተላላፊ በሽታዎችን ስርጭት ለመግታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የዩናይትድ ኪንግደም ተመራማሪዎች ጠቁመዋል።
መረጃው በአውሮፓውያኑ ከ 2006 እስከ 2009 ባሉት ዓመታት ተመሳሳይ አወቃቀር ባላቸው ቫይረሶች ዙሪያ በተደረገ ጥናት የተገኘ ነው። ኮሮናቫይረስ ቀለል ያለ የጉንፋን አይነት ህመም ከሚያስከትሉ ቫይረሶች ነው የሚመደበው።
ታዲያ እነዚህን የቫይረስ አይነቶች፣ ኮሮናቫይረስን ጨምሮ ማለት ነው፣ በቀላሉ በውሀ እና በሳሙና በመታጠብ ብቻ ልንገድላቸው እንችላለን።
ነገር ግን ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ እጃችንን በቀን አስር ጊዜ መታጠባችን ብቻ ከኮሮናቫይረስ ሊጠብቀን አይችልም። ምክንያቱም ቫይረሱ ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚኖረን ንክኪና ትንፋሽ አማካይነት መተላለፍ ይችላል።
እጃችንን መታጠባችን እራሳችንን ከቫይረስ ከመከላከል ባለፈ በዙሪያችን ወዳሉ ሰዎች የማስተላለፍ እድላችንን ይቀንሰዋል።
የእንግሊዝ ማህበረሰብ ጤና ቢሮ ደግሞ እጃችንን በውሃ እና በሳሙና ቢያንስ ለ20 ሰከንድ ያክል መታጠብ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ከምናስበው በላይ ለመቆጣጠር ይረዳል ይላል።
ጄደን ሳንቾ በፀጉር ቁርጡ ምክንያት ተቀጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የምስሉ መግለጫ, እንግሊዛዊው የቦሩሲያ ዶርትመንድ ተጫዋች ጄደን ሳንቾና የቡድን አጋሩ ማኑዌል አካንጂ እንግሊዛዊው የቦሩሲያ ዶርትመንድ ተጫዋች ጄደን ሳንቾ ፀጉሩን ሲቆረጥ የሚታይበት ፎቶ ለቅጣት ዳርጎታል።
ተጫዋቹና ሌላኛው የቡድን አጋሩ ማኑዌል አካንጂ ፀጉራቸውን ሲቆረጡ የሚታዩበት ፎቶ ላይ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አላደረገም ሲል ነው የጀርመን እግር ኳስ አስተዳደር የቀጣው።
ሳንቾ 'ይህ ቅጥ ያጣ ቀልድ ነው' ሲል ቅጣቱን ተችቷል። ሊጉ፤ ተጫዋቾቹ በግልፅ እንደሚታየው የንፅሕና ሕጎችን ጥሷል ይላል።
የ20 ዓመቱ ሳንቾ ቅጣቱን በትዊተር ገፁ ላይ በፅኑ የተቸበትን ፅሑፍ ከቆይታ በኋላ አጥፍቶታል።
ዶርትመንድ ተጫዎቾቼ ምንም ዓይነት ጥፋት አልፈፀሙም ሲል ተከላክሏል።
ፀጉር ቤቶች ጀርመን ውስጥ እንዲከፈቱ ቢፈቀድም ተቆራጭም ሆነ ቆራጭ ጭምብል የማጥለቅ ግዴታ አለባቸው።
ቢሊዬነሩ ቢል ጌትስን ለሴራ ትንተና ያጋለጣቸው ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, ge
ከአምስት ዓመት በፊት ቫንኩቨር የተካሄደው ‘ቴድ’ (TED) መድረክ ላይ ተናገሪ የነበሩት ቢልየነሩ ቢል ጌትስ ነበሩ።
“በቀጣጥ ዓሠርት ዓመታት ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የሚገድለው ጦርነት ሳይሆን ተላላፊ ቫይረስ ነው” ብለው ተናግረዋል።
የዛን መድረክ ንግግራቸውን ቢቢሲን ጨምሮ ብዙዎች ሽፋን ቢሰጡትም፤ ተገቢው ትኩረት አልተቸረውም።
ኮቪድ-19 መሰራጨት ከጀመረ በኋላ በርካቶች ንግግሩን ወደኋላ ተመልሰው እያዳመጡት ነው። ከ64 ሚሊዮን ጊዜ በላይ የንግግሩ ቪድዮ ታይቷል።
ሙሉ ዘገባውን እዚህ ያንብቡ »»» https://www.bbc.com/amharic/news-52947253
