አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመንግሥት ወጪ ተማሪዎችን የሚያስተምረው “መክፈል እንደማይችሉ” ማረጋገጫ ሲያቀርቡ እንደሆነ አስታወቀ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዋና ካምፓስ መግቢያ በር

የፎቶው ባለመብት, addis ababa university

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ በመንግስት ወጪያቸው ተሸፍኖ መማር የሚፈልጉ ተማሪዎች ተቋሙ ለትምህርት የሚጠይቀውን ገንዘብ “ከፍለው መማር እንደማይችሉ” የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው አስታወቀ።

በቀጣዩ የትምህርት ዘመን የሚቀበላቸው ተማሪዎች ብዛት አምስት ሺህ ገደማ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጸው ዩኒቨርስቲው፤ ከዚህ ውስጥ ግማሹ የትምህርት ወጪያቸውን በራሳቸው የሚሸፍኑ እንዲሆኑ ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ባጸደቀው የማቋቋሚያ ደንብ አማካኝነት የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርስቲ የሆነው አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፤ በሁለት ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር እቅድ ይዟል።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሆነው በተሾሙት የቀድሞው የትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ የሚመራው ይህ ሽግግር፤ የተቋሙን ራስገዝነት ከሚያረጋገጥባቸው ተግባራት መካከል አንዱ የሆነውን አዲስ “የተማሪዎች የቅበላ ፖሊሲ” ይፋ አድርጓል።

አዲሱ ፖሊሲ፤ እስከ 2016 ዓ.ም. ድረስ ከትምህርት ሚኒስቴር የሚመደቡለትን የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች ሲያስተምር የቆየው ዩኒቨርስቲ በራሱ ተማሪዎችን መርጦ እንዲቀበል ስልጣን የሚሰጥ መሆኑን የተቋሙ ስትራቴጂክ ኮሚዩኒኬሽን እና አለም አቀፋዊነት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሳምሶን መኮንን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፖሊሲው፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ጋር ሲነጻጸር የተሻለ “መሰረተ ልማት፣ የፕሮፌሰሮች ብዛት፣ ቤተ መጽሀፍት እና ላብራቶሪ” ያለው በመሆኑ “ብቃት ያለው፣ የተመረጠ እና የላቀ ውጤት ያስመዘገበ ተማሪ ብንቀበል ተቋሙ ካለው ሀብት ጋር ተጠቃሚ ይሆናል” የሚል እሳቤን የያዘ እንደሆነ አስረድተዋል።

ከሚቀጥለው ዓመት አንስቶ “ከትምህርት ሚኒስቴር ተመድቦ [ወደ ዩኒቨርሲቲው] የሚመጣ ተማሪ አይኖርም” የሚሉት ዶ/ር ሳምሶን፤ ዩኒቨርስቲው የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን የሚቀበለው አወዳድሮ የራሱን ፈተና ከሰጠ በኋላ በውድድር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ወደ ዩኒቨርስቲው ለመግባት የሚሰጠውን ፈተና የሚያልፉ ተማሪዎች በሁለት አይነት መንገድ ትምህርታቸውን ሊቀጥሉ እንደሚችሉም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። “የራሳችን የተማሪዎች መግቢያ ፈተና አለን። [ተማሪዎች] ለቅድመ ምረቃ እና ድህረ ምረቃ ፈተናውን ተፈትነው ያልፋሉ። [ፈተናውን] ተፈትኖ፣ ተወዳድሮ ያለፈ ተማሪ፤ አንደኛ መንግስት ስፖንሰር ሊያደርገው ይችላል። ሁለተኛ ደግሞ በራሱ ከፍሎ ሊማር ይችላል” ሲሉ አዲሱን የዩኒቨርስቲውን አሰራር ጠቅሰዋል።

እስካሁን ድረስ የነበረው የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች አሰራር የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ያለፉ ተማሪዎች ትምህርት ሚኒስቴር በሚመድባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ውስጥ በሚማሩበት ወቅት ክፍያ ሳይፈጽሙ የመጀመሪያ ዲግሪ ይይዛሉ። በ“ወጪ መጋራት ስርዓት” አማካኝነት የተማሪዎቹን የትምህርት፣ የምግብ እና የመኝታ ወጪ በአብዛኛው በመንግስት የሚሸፈን ሲሆን፤ የተወሰነውን ወጪ ደግሞ ተማሪዎቹ ከተመረቁ በኋላ ይከፍላሉ።

በዚህ አይነቱ መንገድ በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ለመማር ብቸኛው መስፈርት የነበረው የ12ተኛ ክፍል ፈተና ማለፊያ ነጥብ ማስመዝገብ ነው።

የራስ ገዝ አስተዳደርነቱን መተግበር የጀመረው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመንግስት ስፖንሰርሺፕ የሚያስተምራቸው ተማሪዎችን የወጪ አሸፋፈን በምን አይነት መልኩ መሆን እንዳለበት “ከመንግስት ጋር ንግግር እያደረገ” መሆኑን ዶ/ር ሳምሶን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች በምረቃ ስነ ስርዓት ላይ

የፎቶው ባለመብት, addis ababa university

የምስሉ መግለጫ, አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሰኔ መጨረሻ ባካሄደው የ74ኛው ዙር የተማሪዎች ምረቃ ስነ ስርዓት 5,911 ተማሪዎችን አስመርቋል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በመንግስት ስፖንሰርሺፕ አግኝቶ ለመማር ግን የተቋሙን የመግቢያ ፈተና ከማለፍ በተጨማሪ ሌላም መስፈርት መኖሩን አንስተዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመንግስት ወጪያቸው እንዲሸፈንላቸው የሚፈልጉ ተማሪዎችን የሚያስተናግደው፤ ተቋሙ ለማስተማር የሚጠይቀውን ገንዘብ መክፈል የማይችሉ ከሆነ እና ይህንንም የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ ሲችሉ እንደሆነ ዶ/ር ሳምሶን ገልጸዋል።

የዩኒቨርስቲው ስትራቴጂክ ኮሚዩኒኬሽን እና አለም አቀፋዊነት ምክትል ፕሬዝዳንት፤ “እኛ ያስቀመጥነው የመግቢያ ፈተና አለ። እሱን ያለፈ ከፍተኛ ነጥብ ያመጣ ደግሞ [የሚጠየቀውን ክፍያ] መክፈል የማይችል፣ ማስረጃ ማቅረብ የቻለን ተማሪ [መንግስት] ስፖንሰር ያደርጋል ማለት ነው” ሲሉ ፈተናውን ያለፉ ተማሪዎች በሙሉ በመንግስት ወጪያቸው ተሸፍኖ ለመማር ብቁ እንደማይሆኑ ጠቅሰዋል።

በመንግስት ስፖንሰርሺፕ ለመማር ጥያቄ የሚያቀርቡ ተማሪዎች መክፈል እንደማይችሉ ለማረጋገጥ የሚያቀርቡት ማስረጃ “ከሚመለከተው የመንግስት የሚጻፍ አካል” ማረጋገጫ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። ዶ/ር ሳምሶን፤ “የቤተሰብ ደመወዝ አነስተኛ መሆን” አንድ ተማሪ “መክፈል የማይችል” መሆኑን ለመወሰን የሚታይ ሊሆን እንደሚችልም አንስተዋል።

ይሁንና ተማሪዎች የመክፈል አቅም እንደሌላቸው ለማረጋገጥ “ምን አይነት ሰነዶችን ማቅረብ አለባቸው?” የሚለው በዝርዝር እንደሚገለጽ ተናግረዋል።

“ትልቁ ነገር [ተማሪዎቹ መክፈል እንደማይችሉ] ማረጋገጫ ማቅረብ አለባቸው። እውነተኛ እና ትክክለኛ የሆነ ማስረጃ ማለት ነው። እሱን በደንብ የምንለይበት መንገድ ይኖራል” የሚሉት ዶ/ር ሳምሶን፤ “ሀሰተኛ ማስረጃ ያቀረቡ ተማሪዎች “በማንኛውም ጊዜ ስኮላርሺፑን ሙሉ በሙሉ” እንደሚታገድባቸው ገልጸዋል። ይህ አይነቱ ተግባር የህግ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትልም አክለዋል።

በዚህ ስርዓት ውስጥ የማይካተቱ እና ከፍለው የሚማሩ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች ዩኒቨርስቲው ከዚህ ቀደም የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን ክፍያ ለመወሰን በሚጠቀምበት ስሌት መሰረት ለሚማሩት ትምህርት ክፍያ እንደሚጠየቁ ዶ/ር ሳምሶን አስረድተዋል። ከፍለው የሚማሩ ተማሪዎች “በክሬዲት ሀወር እና በኮርስ” ምን ያህል መክፈል እንዳለባቸውም በተመሳሳይ በዝርዝር እንደሚገለጽ አንስተዋል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፤ መስከረም ላይ በሚጀመረው የ2017 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ‘ይቀበላል’ ተብሎ ከሚገመተው አምስት ሺህ ተማሪዎች ውስጥ ግማሽ ያህሉ ከፍለው የሚማሩ እና ቀሪዎቹ ግማሽ ተማሪዎች በመንግስት ወጪ የሚሸፈንላቸው እንዲሆኑ ፍላጎት መኖሩም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል።

ዶ/ር ሳምሶን፤ “እኛ በግል የሚማረው [ተማሪ] ምጣኔ 50/50 ቢሆን እንመርጣለን። ካልሆነ ግን የመንግስቱን ከበለጠ፤ ስኮላርሺፕ ያገኙ፣ ብቃት ያላቸው፣ ሰቃይ ናቸው የምንላቸው ተማሪዎች ስፖንሰርሺፕ አግኝተው ከፍተኛ ከሆኑ ምንም ችግር የለብንም። የማያልፉ ተማሪዎች ካሉ [ቁጥሩ] ከዚያም በተወሰነ መጠን ሊያንስ ይችላል” ሲሉ የተቋሙን ፍላጎት አብራርተዋል።