ጣሊያን ሕገ-ወጥ ሰው አዛዋዋሪዎችን በ30 ዓመት እስር እቀጣለሁ አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጣሊያን ጠቅላይ ሚንስትር ሰዎችን ለሞት እና ለከባድ ጉዳት የሚዳርጉ ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎችን በረጅም ዓመት እስር ለመቅጣት ዕቅድ አወጡ።
ጠቅላይ ሚንስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ ይፋ ያደረጉት ዕቅድ ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች 30 ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፉ ያደርጋል።
የአገሪቱ ባለስልጣናት በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ጣሊያን የሚደረገውን የሰዎች ፍልሰት ለመቀነስ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ ወደ አገሪቱ የሚገቡበትን ሕጋዊ ሁኔታ ለማሻሻል ተስማምተዋል።
የጠቅላይ ሚንስትር ሜሎኒ ካቢኔ ይህን ረቂቅ የወጣው ከአንድ ወር በፊት ስደተኞችን ጭና የነበረች ጀልባ ሰጥማ 72 ሰዎች በሞቱበት አካባቢ ነው።
ጠቅላይ ሚንሰትሯ በካቢኔ ስብሰባው ላይ ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎችን ሰንሰለት ለመበጣጠስ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሯ አገራቸው ጣሊያን በጀልባዎችን ሰዎችን ከሚያዘዋውሩት በተጨማሪ በሦስተኛ አገር ተቀምጠው የስደተኞችን ጉዞ በሚያመቻችሁ ግለሰቦች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደምትወስድ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ሜሎኒ ስደተኞች ደኅንታቸው ተጠብቆ ጣሊያን እንዲገቡ የተሻሻሉ እና ሕጋዊ የጎዞ አማራጮችን ሊከፈቱ ይገባል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሯ ጨምረውም በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ጣሊያን መግባት ያለውን አደጋ ዜጎቻቸውን የሚያስተምሩ አገራት በሕጋዊ መንገድ ዜጎቻቸው ጣሊያን እንዲገቡ የተሻለ ኮታ ይሰጣቸዋል ብለዋል።
የሚንስትሮቹ ስብሰባ በተካሄደበት ኩትሮ የተቋሟ ሰልፍ ተካሂዶ የነበረ ሲሆን አንዳንድ ተቃዋሚዎች ሚንስትሮቹ ይጓዙባቸው በነበሩ ተሸከርካሪዎች ላይ ቁሶችን የወረወሩ ሲሆን ሌሎች ደግሞ “ሕይወታቸውን መታደግ ይቻል ነበር” የሚል ጽሁፍ ይዘው ታይተዋል።
ከአንድ ወር በፊት ሕይወታቸው ላለፉ ስደተኞች የጣሊያን መንግሥት ኃላፊነቱን አልወስድም ያለ ቢሆንም ቀኝ ዘመሙ የሜሎኒ መንግሥት በስደተኞች ላይ የደረሰውን አደጋ ማስቀረት አልያም ደግሞ አደጋው ከደረሰ በኋላ ሰዎችን መታደግ ይችል ነበር የሚል ወቀሳን ሲያስተናግድ ቆይቷል።
የጣሊያን ባለስልጣናት ስደተኞችን ጭና የነበረችው ጀልባ ከሰጠመች በኋላ የ72 ሰዎችን አስክሬን መገኘቱን፣ 79 ሰዎች ከአደጋው መትረፋቸውን እና 30 ሰዎች አሁንም ደረስ የደረሱበት እንደማይታወቅ ገልጸዋል።
በዚህ ጅልባ ላይ ተሳፍረው የነበሩት የአፍረጋኒስታን፣ ፓኪስታን፣ ሶማሊያ፣ ሶሪያ ፣ ኢራቅ እና ኢራን ዜጎች ነበሩ።












