የታይታኒክ ታሳፋሪ ይዞት የነበረው ከወርቅ የተሠራ የኪስ ሰዓት ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተሸጠ

የፎቶው ባለመብት, Henry Aldridge & Sons
ታይታኒክ መርከብ ላይ ከተሳፈሩ ባለጸጋዎች የአንዱ ንብረት የሆነ ከወርቅ የተሰራ የኪስ ሰዓት ለጨረታ ቀርቦ ከመነሻ ዋጋው በስድስት እጥፍ ተሽጧል።
ሰዓቱ የነጋዴው ጆን ጃኮብ አስቶር ሲሆን በዊልትሻየር ጨረታ ቤት በኩል በ150 ሺህ ፓውንድ ይሸጣል ተብሎ ተገምቶ ነበር።
ይሁን እንጂ ሰዓቱ በ1.13 ሚሊዮን ዶላር (900 ሺህ ፓውንድ) መሸጡ ተገልጿል።
ታክስ እና ክፍያ ዋጋዎች ከግምት ሲገቡ ገዥው 1.175 ሚሊዮን ፓውንድ ይከፍላል ተብሏል። የጨረታ አቅራቢው አንድሪው አልድሪጅ አጠቃላይ ወጪውን “የዓለም ክብረ ወሰን” ሲል ገልጾታል።
ለታይታኒክ ቅርስ ከዚህ ቀድም የተከፈለው ከፍተኛ ዋጋ ለቫዮሊን ሲሆን በተመሳሳይ 900 ሺህ ፓውንድ ተሽጧል። በወቅቱ በነበረው የታክስ እና ክፍያ ዋጋው እስከ 1.1 ሚሊዮን ፓውንድ ደርሷል።
ይህ ሰዓቱ ከፍተኛ ዋጋ የወጣበት የታይታኒክ እቃ ለመሆን በቅቷል።
የታይታኒክ ማስታወሻዎች
እአአ በ1912 መርከቧ ስትሰምጥ ኦርኬስትራውን የመራው ሰው የሆነው የቫዮሊን መያዣ ቀደም ሲል በተካሄደ ጨረታው 366ሺህ ፓውንድ ተሽጧል።
ከ280 በላይ የሚሆኑ የመርከቧ ማስታወሻዎች በጨረታ ተሽጠዋል።
ታይታኒክ እአአ በ1912 ከሳውዛምፕተን ወደ ኒውዮርክ ስትጓዝ ነበር በሰሜን አትላንቲክ ውቅያኖስ ከግግር በረዶ ጋር ተጋጭታ የሰጠመችው።
በአደጋው ከአንድ ሺህ 500 በላይ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።

የፎቶው ባለመብት, Henry Aldridge & Sons
ሰዓቱ እና ቡናማው ቫዮሊን መያዣ የቆዳ ቦርሳ በታይታኒክ ደማቅ ታሪክ ውስጥ የተካተቱ የግለሰቦች ንብረቶች ናቸው።
የ47 ዓመቱ አስታር ሚስቱን ማዴሊንን ህይወት እንድትተርፍ በነፍስ አድን ጀልባ ካስቀመጠ በኋላ እና የመጨረሻውን ሲጋራ እያጨሰ ከመርከቧ ጋር ሰምጧል።
ዋላስ ሃርትሌይ በበኩሉ ከሙዚቃ ባንዱ ጋር በመሆን አደጋው ሲከሰት ተሳፋሪዎችን ለማረጋጋት ሙዚቃቸውን እስከመጨረሻው ሲጫወቱ ቆይተዋል።
ሁለቱም እቃዎች የተገኙት የባለቤቶቻቸው አስከሬን ከውሃ ውስጥ በወጣበት ወቅት ነው።
"ከታይታኒክ የተገኙት በርካታ ሰዓቶች አደጋው በደረሰበት ወቅት መሥራት ቢያቆሙም ይሄኛው ሰዓት ተሠርቶ የአስታር ልጅ የሆነው ቪንሰንት ይጠቀምበት ነበር’ ሲሉ የብሪቲሽ ታይታኒክ ሶሳይቲ ሊቀ መንበር ዴቪድ ቤድዳርድ ተናግረዋል።
"ወጣቷ ነፍሰ ጡር ሚስቱን በነፍስ አድን ጀልባ ውስጥ አስገብቷት ሲመለስ እንደማይተርፍ እያወቀ ሰዓቱ በኪሱ መያዙ አስደናቂ ነው" ብለዋል።
መርከቧ ከሰመጠች ከቀናት በኋላ የሃርትሌይ አስከሬን ሲገኝ የቆዳ ቦርሳውን እንዳነገተው ተገኝቷል።
ቤድዳርድ አክለውም “ምንም እንኳን ቦርሳው በውሃ የተጎዳ ቢሆንም በጥሩ ሁኔታ ላይ ሆኖ ተርፏል” ብለዋል።
"ቫዮሊኑ እና ቦርሳው ትክክለኛነቱ ከመረጋገጡ በፊት ለአምስት ወይም ለስድስት ዓመታት ብዙ ጠናቶች ተካሂደውበታል።”

የሄንሪ አልድሪጅ እና ሰን ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት አልድሪጅ ደግሞ “በዚያ መርከብ ላይ ከሁለት ሺህ 200 በላይ ሰዎች አሉ። ስለዚህ ከሁለት ሺህ 200 በላይ ታሪኮች አሉህ ማልት ነው” ብለዋል።
"እነዚያ ሰዎች ሁሉም ለየራሳቸው የሚናገሩት ታሪክ ነበራቸው።”
"ታይታኒክ ከመቼውም በጣም ዝነኛዋ መርከብ እንደሆነችም ሊከራከሩ ይችላሉ።”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እንደ አልድሪጅ ገለጻ ከሆነ “በጣም ብርቅዬ ከሆኑት የታዋቂው የታይታኒክ ማስታወሻዎች” አንዱ ቫዮሊን ነው። እአአ በ2013 ያለ ማስቀመጫ ቦርሳው ለብቻው ተሽጦ በወቅቱ ክብረ ወሰን በሆነ በ900 ሺህ ፓውንድ ተሽጧል።












