በሆንግ ኮንግ በጋራ መኖሪያ ቤት ሕንጻዎች ላይ በተነሳ የእሳት አደጋ ቢያንስ 65 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሆንግ ኮንግ ከተማ በሚገኙ በርካታ የጋራ መኖሪያ ሕንጻዎች ላይ በተነሳ አውዳሚ የእሳት አደጋ ቢያንስ 65 ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ። ከ270 በላይ ሰዎች እስካሁን ያሉበት ያልታወቀ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችም ወደ ጊዜያዊ መጠለያዎች እንዲዘዋወሩ ተደርጓል።
በአንድ አካባቢ በሚገኙ መኖሪያ ሕንጻዎች ላይ የተነሳው እሳት ከ18 ሰዓታት በላይ ለሚሆን ጊዜ ሲግለበለብ ታይቷል። በአስከፊነቱ ባለፉት 60 ዓመታት ከተከሰቱ የእሳት አደጋዎች ቀዳሚ የሆነውን ይህንን ክስተት ለመቆጣጠር ከ800 በላይ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ተሰማርተዋል።
የረቡዕ ምሽቱ እሳት አደጋ የተነሳው በሆንግ ኮንግ በሚገኘው 'ዋንግ ፉክ ኮርት' በተሰኘ ግዙፍ የጋራ መኖሪያ ሕንጻዎች መንደር ነው። ይህ መንደር፤ እያንዳንዳቸው 31 ወለሎችን የያዙ ስምንት የመኖሪያ ሕንጻዎችን የያዘ ሲሆን ከአንድ ሕንጻ በስተቀር በሁሉም ላይ የእሳት አደጋ አጋጥሟል።
በ2021 የወጣ የመንግሥት የሕዝብ ቆጠራ መረጃ እንደሚያሳየው በእነዚህ ሕንጻዎች ላይ በሚገኙት 1,984 አፓርትመንቶች ውስጥ 4,600 ገደማ ነዋሪዎች ይገኛሉ።
ከ42 ዓመት በፊት በ1975 ዓ. ም. የተገነቡት እነዚህ ሕንጻዎች በእድሳት ላይ ነበሩ። ዙሪያቸውም እድሳቱን ለማከናወን በተዘረጉ የቀርከሃ መወጣጫዎች እና አረንጓዴ ባለወንፊት መሸፈኛ ጨርቆች ተከብበዋል።
በአካባቢው የተቀረጹ ቪዲዮዎች እሳቱ በቀርከሃው አማካኝነት በፍጥነት ሲስፋፋ እንደነበር አሳይተዋል። በርካታ ነዋሪዎች ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የሰጡት እማኝነት እንደሚያሳየው እሳቱ በተነሳበት ሰዓት የማንቂያ ደውል አልተሰማም።

የእሳት አደጋው በአስከፊነት መጠኑ ከፍተኛ የሆነው 'ደረጃ አምስት' ምድብ ውስጥ ተቀምጧል። በሆንግ ኮንግ በዚህ ምድብ ውስጥ የወደቀ የእሳት አደጋ የተከሰተው ከ17 ዓመታት በፊት ነበር።
የእሳቱን መነሻ ለማግኘት የተደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ፤ እሳቱ የተስፋፋበት ፍጥነት ያልተለመደ እንደሆነ ማመላከቱን የሆንግ ኮንግ የደኅንነት ኃላፊ ተናግረዋል። በሕንጻው የሚገኙ መስኮቶች የተሸፈኑበት እና በከፍተኛ መጠን የሚቀጣጠለው 'ፖሊስትሪን' የተባለ የግንባታ ግብአት ለእሳቱ መባባስ አንድ ምክንያት ሆኖ ተጠቅሷል።
እሳቱ ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ በአደጋው ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ብዛትን በተመለከተ የሚወጡ ቁጥሮች ቀስ በቀስ እየጨመሩ ነው። የሆንግ ኮንግ ባለሥልጣናት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ የተደረገው የመጨረሻው ቁጥር እንደሚያመለክተው እስካሁን 44 ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል።
40 ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈው በአደጋው ሥፍራ ላይ ሲሆን አራቱ ደግሞ ወደ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ሞተዋል። 45 ሰዎች ደግሞ አስጊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። ከተጎዱት ሰዎች መካከል የእሳት አደጋ ሠራተኞች እንደሚገኙበት ተነግሯል።
ሆንግ ኮንግ ውስጥ በዚህ መጠን የሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ እሳት የተከሰተው ከ63 ዓመት በፊት በአውሮፓውያኑ 1962 ነበር። በወቅቱ በበርካታ ሕንጻዎች ላይ የተነሳው እሳት ለ44 ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከእሳት አደጋው ጋር በተያያዘ ሦስት የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን እና ምርመራ መጀመሩን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። በፖሊስ ከተያዙት ሰዎች ውስጥ ሁለቱ የሕንጻዎቹን እድሳት የሚያከናውነው የኮንስትራክሽን ኩባንያው ዳይሬክተሮች ናቸው። አንዱ ደግሞ የምህንድስና አማካሪ ነው።
የሆንግ ኮንግ ባለሥልጣናት፤ በግንባታ ወቅት ሕንጻን ለመሸፈን የሚውል ባለወንፊት መረብ እና የደኅንነት መጠበቂያ ቁስ ሕንጻዎቹ ዙሪያ አግኝተዋል። እነዚህ ቁሶች እሳትን የሚቋቋሙ እንዳልነበሩም ገልጸዋል። የሕንጻው መስኮቶች ተቀጣጣይ በሆነ የፕላስቲክ ቁስ (ስታይሮፎም) ተሸፍነው ታይተዋል።
የሆንግ ኮንግ ፖሊስ ቃል አቀባይ እንደገለጹት በሚደረገው ምርመራ እሳቱ እንዲነሳ ምክንያት የሆኑ በኩባንያው ኃላፊዎች የተፈጸሙ ድርጊቶች ወይም ቸልተኝነቶች ስለመኖራቸው ማጣራት ይደረጋል።
የኩባንያው ኃላፊ የሆኑ ሰዎች በከፍተኛ መጠን ቸልተኛ በመሆናቸው የተነሳ አደጋው እንደተፈጠረ፣ እሳቱ ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ እንደተስፋፋ እና ከፍተኛ ሞት እንደተከሰተ ለማመን የሚያስችል ምክንያት አለን" ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ እሳቱ የተነሳበት ትክክለኛ ምክንያት አልታወቀም።













