ልክተራ፡ የበይነ መረብ መጽሐፍት ተራ

የፎቶው ባለመብት, SAMUEL GIZAW
ሳሙኤል ግዛው በሙያ አስተዋጽዖ ለማበርከት ያለውን ፍላጎት ለማሟላት አንድ የሥራ ሃሳብ መጣለት።
አርሱም ቦምብ ተራ፣ ጭድ ተራ፣ ጎማ ተራ እና ሚሊተሪ ተራ የመሳሰሉትን መርካቶ መሃል ያሉ የገበያ ቦታ ስያሜ ላይ በመመርኮዝ የመገበያያ መተግበሪያውን 'ልክተራ'ን የመጀመር።
ሳሙኤል ልክተራን የጀመረው ወላጆች ለልጆቻቸው የሚፈልጓቸውን ትምህርታዊ መጽሐፍት በቀላሉ እንዲያገኙ ለማድረግ በማሰብ ነው።
የበይነ መረብ አገልግሎት በኢትዮጵያ አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳን የጀመረው ሥራ አስፈላጊ በመሆኑ 'ኢንተርኔት' በሚቋረጥብትም ጊዜ እንኳን እጅ ላለመስጠት፣ ልክተራ ከዓመት በላይ መጽሐፍትን በሌሎች አማራጮች ለወላጆች ሲያደርስ ቆይቷል።
ስያሜውም የተነሳለትን ዓላማ በሚያመለክት ሁኔታ ተገቢውን እና ትክክለኛውን ነገር ለሚፈልጉት ሰዎች የሚቀርብበት ስፍራ ወይም ተራ እንደማለት ነው።
የልክተራም ዓላማ እንደነዚህ ዓይነት ግልጋሎቶችን ለሰዎች ማድረስ ከሆነ ትክክለኛ መሆን እንዳለበት የሚገልፀው ሳሙኤል "ልክ የሆነ፣ ትክክለኛውን አገልግሎት ነው ለሕዝብ ስናቀርብ የሰዎችን ፍላጎት እና ጥያቄን ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት ነው" ይላል።
ልክተራ አጀማመር
በሌላው ዓለም የሚሰራው የበይነ መረብ መገበያያ ሥርዓትን እንዳለ ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት እንዲሰራ ቢደረግ በተለያዩ ተግዳሮቶች ምክንያት ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል በመገንዘብ፣ ለኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ልክ እንዲሆን በማሰብ ነው ሥራው የተጀመረው።
ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ እያደገ እና እየተሻሻለ እየመጣ ቢሆንም በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ትስስር ሽፋን ገና ከ15 በመቶ ያልበለጠ እና የበይነ መረብ የክፍያ ሥርዓት ገና በጅምር ላይ በመሆኑ ይገኛል።
እንዲህ አይነት ፈጠራን ተግባራዊ እና ውጤታማ ለማድረግ ሕብርተሰቡ በተለምዶ የሚገበያይበትን ሂደት በመከተል ማዘመን ይቻላል በሚል እምነት ነው ስያሜው የተሰጠው - ልክተራ።
ተራ የሚለው ቅጥያ ደግሞ፤ በአፍሪካ ትልቁ የገበያ ስፍራ በመባል የሚታወቅውን የመርካቶን የተለያዩ ክፍሎች ለመሰይም ጥቅም ላይ ከዋለው ስያሜ የተወሰደ ነው። በዚህም አገራዊ የበይነ መረብ የመገበያያ የፈጠራ ሥራ መሆኑን ለማሳወቅ የተደረገ ነው።
ሳሙኤል ኮምፕዩተር ሳይንስ እና ቢዝነስ ያጠና ሲሆን የተማራቸውን ትምህርቶች በማጣመር ነው 'ልክተራን' ያቋቋመው። ጅማሬው ላይ 'አይስ አዲስ' የተሰኘውን የጋራ መሥርያ ቦታን በመጠቀም ሃሳቡን ከወረቀት ባሻገር እውን ሊያደርግ እንደቻለ ይናገራል።
ልክተራ ከበይነ መረብ (ኦንላይን) አቅርቦቱ በተጨማሪ ከበይነ መረብ ውጪ ተጠቃሚዎች በቀላሉ ሊያገኙ የሚችሉት መዘርዝር (ኦፍ ላይን ካታሎግ) በማዘጋጀት መጽሐፍትና ጌሞችን ያቀርባል።
በዋነኝነት ይህን ዓላማን እውን ለማድረግ ሳሙኤልን የገፋፋው በአገሪቱ ያለውን የንባብ ባህል ለማዳበር እና ለማሳደግ አስተዋጽኦ ለማበርከት ካለው ፍላጎቱ የተነሳ እንደሆነ ይናገራል።
"በዋነኛነት ልክተራ ገዢዎችን ከሻጮች ማገናኘት ነው" የሚለው ሳሙኤል፣ ሃሳቡ ሲጠነሰስ በሌላው የዓለም ክፍል ላይ እንዳሉት የዲጂታል መገበያያ መድረኮች እንዲሆን የገበያ ጥናት አካሄዶ የተለያዩ ዕቃዎችን በማስገባት ማሻሻጥ ቢያስብም ቀስ በቀስ ትኩረቱ ወደ መጽሐፍት መሳቡን ይገልጻል።
መፍትሔ ለወላጆች
አልአዛር እና ሰርኪ ከልጆቻቸው ኤልያስ እና ሉሲ ጋር አዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ ነው የሚኖሩት። አብዛኛውን ጊዜያቸውን በሥራ ላይ ስለሚሆኑ ከሥራ ውጪ ያላቸውን ጊዜ ልጆቻቸውን በማስጠናት፣ አብረዋቸው በመጫወት እና በማንበብ ያሳልፋሉ።
ነገር ግን ይህን ሁሉ በሚያደርጉበት ወቅት አንድ ችግር ያጋጥማቸዋል፤ ይህም የሚፈልጉትን መጽሐፍት እና ጌምችን በቀላሉ ለማግኘት አለመቻል ዘወትር የሚገጥማቸው እንቅፋት ነበር።
እነዚህን አስፈላጊ ነገሮች ፈልጎ ለማግኘት የሚሆን ጊዜ ስለሌላቸው፣ ለልጆቻቸው ትምህርትና መዝናኛ የሚሆኑ መጽሐፍትና ሌሎችንም ነገሮች ማቅረብ ይቸገራሉ።
አሁን አልአዛር እና ሰርኪ በልክተራ ከተመዘገቡ በኋላ የሚፈልጉትን ነገር በመምረጥ መግዛት እንደሚፈልጉ ያረጋግጣሉ። ከዚያም በአቅራቢያቸው ከሚገኙ መደብሮች መካከል ትዕዛዝ ያስቀምጣሉ።
ልክተራ ደግሞ በመረጡት መደብሮች አማካይነት ያዘዙትን መጽሐፍት እና መጫወቻዎችን ያደርስላቸዋል። ከዚያም እነሰርኪ በ48 ሰዓት ውስጥ ወደ መረጡት እና በአቅራቢያቸው ካለ መደብር ክፍያ ፈጽመው ያዘዙትን መውሰድ ይችላሉ።
አሠራራቸው ቀላል እንደሆነ የሚናገረው ሳሙኤል “በስፋት የማይገኙ መጽሐፍትን ከተለያዩ ሱቆች ጋር በመጣመር ለወላጆች እናደርሳለን። በመተገበሪያችን የሚፈልጓቸውን ትምህርታዊ የሆኑ መጸሐፍትን ያዙናል፣ የሚኖሩበትንም አካባቢ ያሳውቁናል እኛም የሚፈልጉበት ድረስ እናቀርብላቸዋለን” ይላል።

የፎቶው ባለመብት, SAMUEL GIZAW
የት ማግኘት ይቻላል?
ልክተራ በተለይ በትምህርት መጀመሪያ ወቅት የወላጆች ዋነኛ ራስ ምታት የሆነውን የመማሪያ መጽሐፍት የማግኘት ፈተናን ለማቃለልም አማራጭ መንገድንም አበጅቷል።
በየክፍለ ከተማው በሚገኙ በትምህርት ቤቶች ወይም በመኖሪያዎች አቅራብያ በሚገኙ ኪዮስኮች ወይንም አነስተኛ መደብሮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ መሥሪያ ቤቶች፣ ሆቴሎች እና በሌሎችም ቦታዎች የመጽሐፍት ዝርዝሮችን አመቻችቷል።
በዚህም ወላጆች የሚፈልጓቸውን መጽሐፍት ቀጥታ በልክተራ ዌብ ሳይት ላይ ወይም በስልክ በመደወል የሚፈልጉትን መጽሐፍት በማዘዝ የሚፈልጉበት ቦታ ለማድረስ የሚያስችል መንገድን አዘጋጅቷል።
ለጊዜው አገልግሎቱ በከተሞች ውስጥ በተወሰነ ቦታ ብቻ ይገኛል። ከከተሞች ራቅ ባሉ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሰዎች በሚችሉት አቅም እና መድረስ በሚችሉባቸው ቦታዎች በሚገኙ ኪዮስኮች ወይንም አነስተኛ መደብሮች እና ሌሎች ሰዎች በብዛት የሚበዙባቸው ትምህርት ቤቶች፣ መሥሪያ ቤቶች እና ሆቴሎችን በመሳሰሉ ተቋማት ጋር ይሰራሉ።
እነዚህ ተቋማትም ለልክተራ እንደ ወኪል እንዲሰሩ ለማድረግም የአቅርቦት ዝርዝራቸውን በማስቀመጥ መጽሐፍት ፈላጊዎች የሚፈልጉት እንዲያዙ ያደርጋሉ።
አገልግሎቱ እና ክፍያ
በዚህ አገልግሎት ተጠቃሚዎች መጽሐፍትን ያለተጨማሪ ክፍያ በዋጋቸው የሚያገኙ ሲሆን፣ ሆኖም ግን አንዳንድ ከገበያ የጠፉ እና በቀላሉ መገኘት የማይችሉ መጽሐፍት ላይ የተወሰነ ጭማሪ በማድረግ ያቀርባሉ።
እንዲሁም ወኪል መደብሮች በሌሉባቸው ስፍራዎች ላሉ ተጠቃሚዎች ትዕዛዛቸውን ቤታቸው ድረስ ለማቅረብ የማድረሻ (ዴሊቨሪ) ዋጋ ያስከፍላሉ።
እንደሚታወቀው የኦንላይን የመገበያያ (ኢኮሜርስ) ካለው የተለያየ አሰራር አንደኛው ደንበኛን ከአቅራቢ ጋር ማገናኘት ነው። ልክተራም በዚህ ሂደት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት “የደንበኞቻችንን ያሉበትንና ፍላጎታቸውን በመከተል፣ በአቅራቢያቸው ሊገኙ በሚችሉ ወኪሎች አማካይነት የሚፈልጉትን እናቀርባለን” ብሏል ሳሙኤል።
በተጨማሪም ሻጮች በልክተራ አማካይነት በቀላሉ ካሉበት ቦታ ሆነው ምርቶቻቸውን እንዲሸጡ ማመቻቸታችን እንዲሁም ገዢ እና ሻጭ የማቀራረብ ዋናው የሥራቸው አካል ነው።
ተግዳሮቶች
ልክተራ እንደማንኛውም ጀማሪ ንግድ (ስታርታፕ ካምፓኒ) ዋንኛው ችግሩ በጀት ነው ሳሙኤል። ይህም አገልግሎታቸውን በየቦታው ለማዳረስ እና ለማስተዋወቅ፣ የተለያዩ ባለሙያዎችን በቋሚነት ለመቅጠር፣ የቴክኖሎጂ እና ሌሎች ዘመናዊ አሠራሮችን ለመዘርጋር እንዳይችሉ ተግዳሮት ነው ይላል።
ሕልሙን እውን ለማድረግ እየተሯሯጠ በነበረበት ወቅት ሁሉም አልጋ በአልጋ እንዳልነበር የሚያስታውሰው ሳሙኤል ገንዘብ በጅተው አብረውት ለመስራት የሚችሉ ሰዎች ለማግኘት በጣም ከባድ ነበር።
በተለይ የዕለት ተዕለት ሥራውን ለማካሄድ በ'ኢንተርኔት' ምክንያት "ሥራው ከባድ ይሆናል ተብሎ ይታሰብ ስለነበር፣ በዚህ መስክ ላይ ለመሰማራት ፈቃደኛ ሰው አልነበረም" በማለት ልክተራን ለመጀመር ጊዜ እንደፈጀ ያስረዳል።
ልክተራ ጀማሪ የንግድ ተቋም ነው፤ ለዚህ ደግሞ ሥራውን የማንቀሳቀሻና የማስፋፊያ በቂ ገንዘብ ቢያስፈልገውም በታሰበው መጠን እየሰራ አይደለም። ነገር ግን ልክተራ ሥራዎች በቀላሉ ተጀምረው እየሰፉ መሄድ የሚችሉ መሆናቸውን ለማሳየት ምሳሌ የሚሆን ነው።
ሳሙኤል ሥራውን የጀመረው ከ‘ሪች ፎር ቼንጅ ኢትዮጵያ’ ባገኘው የ40 ሺህ ብር ድጋፍ ሲሆን፣ ከዚያ ውጪ የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም ራሱን በራሱ ከሽያጭ እና በተጓዳኝ ሥራ ከሚገኝ ገቢ እየደገፈ እንዲሰራ እያደረገ ይገኛል።
ልክተራ ለጊዜው አነስተኛ ቢሆንም የሥራ ቦታ አለው፤ በአሁኑ ጊዜ ከተለያዩ መጽሐፍት አቅራቢዎች፣ ደራሲያን እና ወደ 30 ከሚጠጉ ወኪሎች ጋር እየስራ ነው። ለዚህም ሦስት ቋሚ እና ጊዜያዊ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ 12 በተለያየ ሙያ የሚያግዙ በጎ ፈቃደኞች አሉት።
የወደፊት አላማ
ይህ በጅማሬ ላይ ያለ ሥራ ለወደፊት ትልቅ ዓላማን ሰንቆ ለማደግ እየጣረ ይገኛል።
በሂደት እየጎለበተ ሲሄድም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ ገጠር ከከተማ ሳይለይ ነዋሪዎች ትምህርታዊ መጽሐፍትንና ሌሎችንም በቀላሉ በአቅራቢያቸው ሊያገኟቸው የማይችሉ መጽሐፍትን ማቅረብ ዓላማው ነው።
ይህ ሥራ በየጊዜው በኢትዮጵያ ካለ ወቅታዊ እና ነባራዊ ሁኔታ ጋር እየተጣጣመ የሚሄድ፣ 'ልክ የሆነ' ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ በማኅበረተሰቡ ተቀባይነት ያለው የበይነ መረብ (ኦንላይን) የመገበያያ መፍትሄ እንዲሆን ሳሙኤል እየጣራ ነው።
ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት የመጽሐፍት ዓይነቶች፣ ብዛታቸውና የሚገኙባቸው ቦታዎች ውስን በመሆኑ ተደራሽነቱን ለማስፋት እና ወደፊት ከመጽሐፍት ውጪ ትምህርታዊ ሆኑ መገልገያ ዕቃዎችንም የማካተት ዓላማ አለው።
"እንደ አገር አሁን ባለንበት ደረጃ የኢንተርኔት ክፍያ ለመፈፀም አስቸጋሪ በመሆኑ፤ 'የአማዞን' አይነት አገልግሎትን ለማስጀመር በጣም ከባድ ነው። እንደ አጀማመራችን ግን ወደፊት ከአማዞን ጋር መሥራት የምንችልበትን ዕድል እያሰፋን ነው እንሄዳለን።"
ይህም በሂደት ተጠናክሮና አድጎ ከኢትዮጵያ ባሻገር በሌሎችም የአፍሪካ አገራት ውስጥ ሥራውን የማስፋፋት ዓላማን ይዟል - ልክተራ።












