የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ማክሮን ብሔራዊ አገልግሎትን በድጋሚ ተግባራዊ አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፈረንሣይ መንግሥት ለ16 ዓመት ታዳጊዎች ብሔራዊ አገልግሎትን መልሶ ለማምጣት ዕቅድ አወጣ።
በፈረንሣይ ወጣቶች ዘንድ የዜግነት ግዴታን እና ብሔራዊ አንድነትን ለማሳደግ በማለት ኢማኑኤል ማክሮን እንደሚተገብሩት ለፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ ያቀረቡት ሃሳብ ነበር።
አንዳንዶች ግን ያስገኛል ስለተባሉት ጥቅሞች እርግጠኛ አይደሉም።
አዲሱ ብሔራዊ አገልግሎት ሁሉንም የ16 ዓመት ታዳጊዎችን የሚመለከት ሲሆን በሁለት የተለያዩ ደረጃዎች ይከፈላል ተብሏል።
በሁለት የተከፈለ ብሔራዊ አገልግሎት
የመጀመሪያው ምዕራፍ በግዴታ የሚሰጥ እና ለአንድ ወር በምደባ የሚከናወን ሲሆን በዜግነት ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል። ይህም መንግስት "ወጣቶች አዲስ ትስስር እንዲፈጥሩ እና በህብረተሰቡ ውስጥ ሚናቸውን እንዲያሳድጉ ያስችላቸዋል" ብሏል።
በፈቃደኝነት ማስተማር እና ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር አብሮ መሥራትን ጨምሮ ከፖሊስ፣ ከእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኞች ወይም ከሠራዊቱ ጋር የተለመደውን ወታደራዊ ዝግጅት ከመስጠት ጎን ለጎን ሌሎች አማራጮችም እንዲካተቱ ከተያዙት መካከል ናቸው።
ሁለተኛው ምዕራፍ ቢያንስ ከሦስት ወር እና እስከ አንድ ዓመት የሚፈጅ በፈቃደኝነት የሚደረግ ምደባ ሲሆን ወጣቶች "ከመከላከያ እና ከደህንነት ጋር በተገናኘ" እንዲያገለግሉ ይበረታታሉ። ከቅርስ፣ ከአካባቢ ጥበቃወይም ከማህበራዊ ሥራዎች ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የበጎ ፈቃድ ስራዎችን ማከናወን ይችላሉ ተብሏል።
የተሸረሸረው እቅድ
ማክሮን መጀመሪያ ላይ ያሰቡት አይነት ፕሮግራም አይደለም።
ሃሳቡን ለመጀመሪያ ጊዜ እአአ በ 2017 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወቅት ሲያቀርቡት ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 21 መካከል ያሉ ሁሉም የፈረንሣይ ዜጎች ቢያንስ ለአንድ ወር ያህል አነስተኛ “የወታደራዊ ሕይወት ልምድ” እንዲኖራቸው የሚገደዱበት ወታደራዊ አገልግሎት ዓይነት ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሁን ዕቅዱ በለሰለሰ እና ሁለንተናዊ ብሔራዊ አገልግሎት እየተባለ ወደሚጠራው ደረጃ እንዲሰፋ ተደርጓል። ለዚህ ምክንያት ከሆኑት አንዱ ብዙ ወጪ በማስወጣት የአገሪቱ ጦር ወጪ ላይ ጫና ይኖረዋል በሚል ስጋት ነው።
ሆኖም ግን ፕሮግራሙን ለማስፈጸም አሁንም በዓመት 1.8 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስወጣ ተገምቷል።
የማክሮን ዓላማ ምንድነው?
የአዲሱ ብሔራዊ አገልግሎት ዓላማ ወጣት ፈረንሳዊያንን በአገሪቱ ህይወት ውስጥ እንዲሳተፉ ለማበረታታት እና ማህበራዊ ትስስርን ለማሳደግ ነው ተብሏል።
ከሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ ፕሮግራሙን ለማስጀመር በማሰብ ምክክር ከወዲሁ ይጀምራል።
ከህጋዊ ጉዳዮች ጎን ለጎን አሁንም ግን ብዙ ዝርዝር ጉዳዮች ይቀራሉ።
ዕቅዱን ለመፈተሽ የተቋቋመው ቡድን ከብሔራዊ መከላከል ጉዳይ ውጭ አንድን የህብረተሰብ ክፍል ከቤት አርቆ እንዲያሳልፍ ማስገደድን የፈረንሳይ ህገ መንግስት እንደሚከለክል በመጥቀስ አስጠንቅቋል።
ተቀባይነት ያለው ሃሳብ ነው?
ይፋ ከመደረጉ በፊትም 14 የወጣት አደረጃጀቶች በፕሮጀክት ውስጥ ለመሳተፍ መገደዳቸውን በመቃወም በእቅዱ ውስጥ ያለውን “ወጥነት አለመኖር” ተቃውመዋል። “ግዳጁን መምረጥም ልክ እንደ ግዳጁ አስፈላጊ ነው" ሲሉ ተከራክረዋል። ወጣቶች የመምረጥ ነጻነታቸውን መጠቀም እንዲችሉም ጠይቀዋል።
በመጋቢት በተካሄደው የዩጎቭ የሕዝብ አስተያየት መሠረት 60 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የሃሳቡ ደጋፊ ነው። የወጣቶች ድጋፍ ግን ከግማሽ በታች ሆኗል።
ማክሮን በብሔራዊ አገልግሎት ያላገለገሉ የመጀመሪያው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ናቸው። እአአ በ 1996 ማክሮን የ18 ዓመት ወጣት በነበሩበት ጊዜ በወቅቱ የነበረው ብሔራዊ አገልግሎት ቀርቷል ።
በዓለም ዙሪያ ብሔራዊ አገልግሎት የሚሰጥባቸው አገራት
- ሰሜን ኮሪያ ረጅም ወታደራዊ አገልግሎት በግዴታ የምትተገብር አገር ስትሆን ለወንዶች 11 ዓመት፤ ለሴቶች ደግሞ ሰባት ዓመት መሳተፍ ግዴታ ነው።
- የእስራኤል የግዴታ ወታደራዊ አገልግሎት ለወንዶች ሦስት ዓመት እና ለሴቶች ሁለት ዓመት ነው።
- የስካንዲኔቪያ አገሮቹ ስዊዘርላንድ፣ ኦስትሪያ እና ግሪክ አሁንም የግዴታ ወታደራዊ አገልግሎት ካላቸው የአውሮፓ አገሮች መካከል ይጠቀሳሉ።
- ቻይና በንድፈ ሃሳብ ብቻ ያለ የውትድርና ግዳጅ አላት። በጎ ፈቃደኝትነት የሚቀላቀሉ ወታደሮቿን ከዓለም ትልቁን ጦር እንድትገነባ ስላደረጓት በግዳጅ ተፈጻሚ አድረጋው አታውቅም።
- ሕንድ በብሪታንያ አገዛዝ ወቅት አንኳን የግዴታ ወታደራዊ አገልግሎት ኖሯት አያውቅም። በበጎ ፈቃደኞች የተዋቀረ በዓለም ሁለተኛውን ትልቅ ሠራዊት ገንብታለች።
- በዩናይትድ ኪንግደም ለመጨረሻ ጊዜ ወንዶች በግዳጅ የጠራችው እአአ በ1960 ሲሆን አሜሪካ ደግሞ በ1973 ነበር።
- ኢራን ለወንዶች የሁለት ዓመት የግዴታ አገልግሎት አላት። በቤት ውስጥ ያሉ ብቸኛ ወንዶች፣ ዶክተሮች እና የእሳት አደጋ ተከላካዮች ግዳጁ አይመለከታቸውም።












