ሊጠናቀቅ ቀናት በቀረው አጎዋ ምክንያት ሕይወታቸው እንጥልጥል ላይ ያለው አፍሪካውያን ሠራተኞች

የጆአን ዋምቡኢ ጨርቅ እየሰፋች
የምስሉ መግለጫ, የጆአን ዋምቡኢ ቤተሰቦች ሕይወት የተመሠረተው በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሠርታ በምታገነው ደመወዝ ላይ ነው

በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ውስጥ በሚገኘው 'ሾና ኢፒዜድ' የጨርቃ ጨርቅ ፍብሪካ ውስጥ ውጥረት ነግሷል።

ለወትሮው ፋብሪካው ከፍተኛ የስፌት ማሽኖች በሚያወጡት ድምጽ እና በሠራተኞች የጎንዮሽ ሹክሹክታ የተሞላ ነበር። ዛሬ ግን በፋብሪካው የሚስተጋባው የአሜሪካ ከቀረጥ ነጻ የንግድ ዕድል ሊቋረጥ መሆኑ የፈጠረው ጭንቀት እና ውጥረት ነው።

'አፍሪካን ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት' (አጎዋ) ተብሎ የሚጠራው እና ላለፉት 25 ዓመታት የአፍሪካ አገራት ምርቶቻቸውን ከቀረጥ ነጻ ለአሜሪካ ገበያ እንዲያቀርቡት የፈቀደው አሠራር በመጪው ማክሰኞ ይጠናቀቃል።

ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የቆየው ይህ ፖሊሲ፤ አዳዲስ ታሪፎችን በመጣል ሪከርድ ከያዘው የትራምፕ አስተዳደር ዕሳቤ ጋር የሚስማማ አይደለም።

የበርካታ የአፍሪካ አገራት ልዑካን የዕድሉ የቆይታ ጊዜ እንዲራዘም የሚያስችል ድርድር ለማድረግ በሚል ወደ አሜሪካ ተጉዘዋል። እንስካሁን ድረስ ግን ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ አልያም ከሽፎ እንደሆነ በግልጽ አልታወቀም።

የአሜሪካ እና አፍሪካ የኢኮኖሚ ግንኙነት ማዕዘን ተደርጎ የሚቆጠረው አጎዋ የተጀመረው፤ በአህጉሪቱ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ፣ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር እንዲሁም በርካታ አገራትን ከድህነት እንዲወጡ ለማድረግ ነበር።

አጎዋ የተመሠረተው 'እርዳታን በንግድ መተካት' በሚል ፍልስፍና ላይ ነው።

ይህ ከቀረጥ ነጻ እድል እንደ ኬንያ እና ሌሴቶ ባሉ አገራት እጅጉን ጠቃሚ መሆኑን አስመስክሯል። እንደ 29 ዓመቷ ጆአን ዋምቡኢ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ዕጣ ፋንታን የሚወስን ጉዳይም ሆኗል።

የአጎዋ የቆይታ መጠናቀቅ ለጆአን መርዶ ነው። የዕድሉ መቋረጥ ከሥራ እንድትሰናበት ሊያደርጋት ይችላል።

ከስድስት ወር በፊት 'ሾና ኢፒዜድ' የተባለውን ፋብሪካ የተቀላቀለችው ጆአን፤ ድርጅቱ ለአሜሪካ ገበያ ብቻ የሚያመርታቸውን የስፖርት ትጥቆች በመስፋት ሥራ ላይ ተሰማርታለች። የእነ ጆአን ቤት ዋነኛ የገቢ ምንጭ ፋብሪካው የሚከፍላት ደመወዝ ነው።

የአራት ዓመት ልጇን የምታሳድገው፣ ኮሌጅ የሚማሩ ሁለት እህቶቿን የምታግዘው እና እናቷን የምትጦረው በዚህ ደመወዝ ነው።

ከሥራ መሰናበት የሚጎዳው የእሷን ሕይወት ብቻ እንዳልሆነ ትናገራለች።

የስፌት ማሽን ላይ ቁጭ ብላ እጅ እና እግሯን እያንቀሳቀሰች ሁለት ጨርቆችን አንድ ላይ የምትሰፋው ጆአን፤ "አጎዋ የሚያበቃ ከሆነ ወደየት እንሄዳለን" ስትል ፍርሃት በተጫነው ድምጽ ትጠይቃለች።

ለእርሷ መደበኛ ደመወዝ ተከፋይ መሆን ከገቢ ከማግኘት በላይ ነው። ሥራ ማግኘት የክብርም ጉዳይ ነው። የትምህርት ቤት ክፍያዎችን እንድትከፍል፣ የቤታቸውን ጠረጴዛ ላይ ምግብ ማቅረብ እንድትችል እና ስለ ወደፊት ተስፋ እንድትሰንቅ ያደረጋት ይህ ሥራ ነው።

የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሠራተኞች በስራ ላይ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"[የሥራው መቋረጥ] በከባዱ ይጎዳኛል። አዲስ ሥራ እያፈላለግኩ ነው። ኬንያ ውስጥ ሥራ ማግኘት ከባድ ነው፤ በጣም ከባድ" ትላለች።

የኬንያ አልባሳት ኢንዱስትሪ እንዲህ የተስፋፋው የአጎዋ ዕድል ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ ነው።

ኬንያ በ2024 ብቻ 470 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ አልባሳትን ወደ አሜሪካ ልካለች። በዚህም ምንክያት 66 ሺህ ቀጥተኛ የሥራ ዕድሎች እንደተፈጠሩ እና ከእነዚህ ውስጥም ሦስት አራተኛው የሚሆነው የሥራ ዕድል የተያዘው በሴቶች እንደሆነ 'ኬንያ ፕራይቬት ሴክተር አላያንስ' የተባለው የግል ዘርፍ ተዋንያን ኅብረት መረጃ ያመለክታል።

በኬንያ ከባድ ኢኮኖሚ ሁኔታ ምክንያት ሥራ ለማግኘት እየተቸገሩ ላሉት ወጣቶች ወሳኝ የሥራ ዕድል ምንጭ የሆኑት እንደ 'ሾና ኢፒዜድ' ያሉ ፋብሪካዎች ናቸው።

ጆአን፤ "እዚህ ያሉት አብዛኛዎቹ ከጎዳና ላይ የመጡ ናቸው" ትላለች። "የአደንዛዥ እጽ ሱሰኛ ነበሩ። እዚህ ተለውጠዋል፤ አጎዋ የሚያበቃ ከሆነ ወደዚያ ሊመለሱ ይችላሉ" ስትልም ስጋቷን ትገልጻለች።

ሾና ኢፒዜድ የሚቀጥራቸው አዲስ ሠራተኞች ክህሎት ያላቸው እንዲሆኑ አይጠብቅም። ኩባንያው የሥራ ዕድል የሚሰጣቸውን ሰዎች ያሰለጥናል።

የአጎዋ ዕጣ ፋንታ በግልፅ አለመታወቁ ኩባንያው የሚያመርታቸውን አልባሳት ብዛት ከአሁኑ እንዲቀንስ አድርጎታል።

ፋብሪካው በመደበኛው ወቅት ግማሽ ሚሊዮን ገደማ አልባሳትን በየወሩ ያመርት ነበር። ደንበኞች የረዥም ጊዜ ትዕዛዝ ለመስጠት እያንገራገሩ መሆኑን ተከትሎ ግን በዚህ ዓመት የምርት ብዛቱን በአንድ ሦስተኛ ቀንሷል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከወራት በፊት በርካታ አገራት ላይ ቢያንስ 10 በመቶ ታሪፍ መጣላቸውን ተከትሎ የኬንያ የጨርቃ ጨርቅ ምርት ሽያጭ ወርዷል።

አጎዋ እንዲቀጥል ቢደረግም እንኳን በዚህ ምክንያት የቀነሰው የግዢ ፍላጎት ወደ ነበረበት አይመለስም፤ ቢያንስ ግን የአገሪቱ ምርቶች ወደ አሜሪካ ሲገቡ ተጨማሪ ታሪፍ እንዳይጣልባቸው ያደርጋል።

የፋብሪካው ዳይሬክተር አይዛክ ማሉኪ፤ "ዕድሉ የማይራዘም ከሆነ ሠራተኞችን ወደ ቤታቸው ልንመልስ እንችላለን፤ ድርጅቱን ሊዘጋ ይችላል" ይላል።

የሾና ኢፒዜድ ፋብሪካ ዳይሬክተር አይዛክ ማሉኪ
የምስሉ መግለጫ, አጎዋ የማይራዘም ከሆነ ፋብሪካው ሠተራኞችን ሊያሰናብት እና ሊዘጋ እንደሚችል የሾና ኢፒዜድ ፋብሪካ ዳይሬክተር አይዛክ ማሉኪ ይናገራል

"ሰዎች እዚህ ለማቆየት የሚያስችል በቂ ሥራ ካላገኘን ሌላ አማራጭ አይኖረንም" ሲልም ያስረዳል።

700 ሠራተኞችን የቀጠረው ሶና ኢፒዜድ ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ፋብሪካውን ለመገንባት 10 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርጓል።

"ዕድሉ የማይራዘም ከሆነ የ10 ሚሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት ሲከስር እንመለከታለን" ሲል ማሊኩ በጭንቀት ይናገራል።

ይህ አይነቱ ፍርሃት ያለው ኬንያ ውስጥ ብቻ አይደለም። ከ30 በላይ የአፍሪካ አገራት ከጨርቃ ጨርቅ እስከ የግብርና ምርት ያሉ ከ6,000 በላይ ሸቀጦችን በአጎዋ አማካኝነት ወደ አሜሪካ እየላኩ ይልካሉ።

አሜሪካ የቀረጥ ነጻ ፕሮግራም ሥራ እንዲፈጠር፣ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ እና የአፍሪካ አገራት ኢኮኖሚ በዓለም የንግድ መድረክ ጠንካራ አቋም እንዲኖራቸው እንዳደረገ ይነገርለታል።

አፍሪካ ተደራዳሪዎች ወደፊት ሌላ ስምምነት ላይ በሚደርሱበት ሰዓት ግን የሚከተሉንት አካሄድ በድጋሚ ማጤን እንደሚጠበቅባቸው የንግድ ፖሊስ ባለሙያዋ ቴኒኦላ ታዮ ትገልጻለች።

"የአፍሪካ አገራት ከአሜሪካ ምን እንደሚፈልጉ እና ምን እንደሚያቀርቡ በእጅጉ አስበው ሊደርሱበት ይገባል። ምክንያቱም በምላሹ ገበያው እንዲያገኙ የሆነ ነገር ማቅረብ አለባቸው" ትላለች።

የአፍሪካ መሪዎች ዋሽንግተን የአጎዋን ዕድል እንድታራዝም በጽኑ ሲወተውቱ ከርመዋል። ባለፈው ሳምንት በነበረው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይም የንግድ ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ ነበር።

የኬንያ የንግድ ሚኒስትር ሊ ኪንያንጁኢ አገራቸው የአጎዋ ዕድል ቢያንስ ለአጭር ጊዜ እንዲራዘም ግፊት እያደረገች መሆኗን አስታውቀዋል።

ቱታ ሱሪዎች ተቀመጡበት ጠረጴዛ ላይ እየሰራች ያለች ሠተራኛ
የምስሉ መግለጫ, ቱታ ሱሪዎች ተቀመጡበት ጠረጴዛ ላይ እየሰራች ያለች ሠተራኛ

"ሽግግር ሜካኒዝሞች ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል አጎዋን ማራዘም በጣም ጥሩ ሐሳብ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥም ግን ኬንያ ከአሜሪካ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ለመፈራረም እየጣረች ነው።

ለአፍሪካ የተሰጠው ከቀረጥ ነጻ ዕድል ቢያንስ ለአምስት ዓመታት እንዲራዘም እየጠየቁ ያሉት የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ፤ በ2025 መጨረሻ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር የንግድ ስምምነት እንደምትፈራረም ባለፈው ሳምንት አስታውቀዋል።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳም በተመሳሳይ፤ ሁኔታው በአገራቸው ላይ ከባድ መዘዝ እንደሚያስከትል አስጠንቅቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳላ ኬንያ እና ሌሎች አገራት በአሜሪካ ላይ ያላቸውን ጥገኛነት ለመቀነስ በማሰብ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን እያፈላለጉ ነው።

የንግድ ፖሊሲ ባለሙያዋ ታዮ፤ ይህ እንቅስቃሴ የአፍሪካን ነጻ የንግድ ቀጠናን መጠቀምን ሊያካትት እንደሚገባ ታሳስባለች።

"አፍሪካውያን እርስ በርሳቸው በሚነግዱበት ጊዜ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ዕቃዎች ለማምረት ይጥራሉ። ጥሬ ዕቃዎችን ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ ግብአት ተጨምሮ የተመረቱ ሸቀጦችን ለማምረት ይጥራሉ" ትላለች።

ግን ይህ ሁሉ ጊዜ ይወስዳል። እንደ ጆአን ላሉት ሠራተኞች የዲፕሎማሲ እና የንግድ ድርድር መንገዶች የሚጓዙበት ፍጥነት ቤተሰብን መመገብ ከሚጠይቀው የዕለት ተዕለት ጥድፊያ ጋር የሚጣጣም አይደለም።

ጆአን ለኬንያ እና አሜሪካ መንግሥታት ማቅረብ የምትፈልገው አንድ ምክር አላት፤ "ለወጣቶች ተጨማሪ ዕድሎችን ስጡ" የሚል።

"ሐሳቦች እና ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ተነሳሽነት አለን። ያለንን አቅማችንን ለማሳየት የምንፈልገው ድጋፍ ብቻ ነው" ትላለች።