ቻይና የከፋ ድህነትን ከግዛቷ ማስወገዷን አወጀች

የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂፒንግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ አገራቸውን "በተዓምርዊ" ሁኔታ ከከፋ ድህነት መውጣቷን ተናገሩ።

ፕሬዝዳንቱ መንግሥታቸው ባለፉት ስምንት ዓመታት ከ100 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ከድህነት ማውጣት መቻሉን ገልፀዋል።

ዢ ጂንፒንግ ቤይጂንግ ውስጥ በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት "የተሟላ ድል" በማለት ስኬቱን አንቆለጳጵሰው "በታሪክ ውስጥ የሚመዘገብ" ብለውታል።

ነገር ግን ይህ የፕሬዝዳንቱ ንግግር ያልተዋጠላቸው ባለሙያዎች ድህነት በቻይና እንዴት እንደተለካ ጠይቀዋል።

በቻይና የከፋ ድህነት ተብሎ የሚገለፀው በዓመት ገቢው ከ620 ዶላር በታች የሆነ ግለሰብ ነው።

ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው "የከፋ ድህነትን የማስወገድ ተግባሩ ተጠናቅቋል" ብለዋል።

አሁን ባለው መስፈርት በገጠራማ የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ 98.99 ሚሊዮን ድሆች በሙሉ ከድህነት ወጥተዋል፤ 832 በድህነት የተጎዱ አካባቢዎች እና 128 ሺህ መንደሮች ደግሞ ከድህነት ዝርዝር ውስጥ ስማቸው ተፍቋል" ሲሉ አክለዋል።

ዢ ጂንፒንግ ወደ ስልጣን ከመጡበት 2012 (እኤአ) ጀምሮ በገጠር ያለን ድህነትን ማስወገድ ቁልፍ ተግባራቸው አድርገው ሲሰሩ ነበር።

ቻይና ባለፈው ዓመት የመጨረሻዎቹን ድሃ የተሰኙ አካባቢዎችን ከድህነት ዝርዝር ውስጥ ስማቸውን አንስታለች።

በዚህም የተነሳ ቻይና በ2020 የከፋ ድህነትን ማስወገድ ችላለች።

ዛሬ፣ ሐሙስ በተካሄደ ክብረ በዓል ላይ ዢ ጂንፒንግ ድህነትን በመዋጋት ተግባር ውስጥ ለተሳተፉ አካላት ሜዳሊያ ሸልመዋል።

ነገር ግን ባለሙያዎች ቻይና ድህነትን የምትበይንበትን መስፈርት ዝቅ አድርጋ አስቀምጣለች፤ አሁንም በድሃ አካባቢዎች ተጨማሪ ሃብት ማፍሰስ ያስፈልጋል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በቻይና አንድ ሰው የከፋ ድህነት ውስጥ ይኖራል ለመባል የቀን ገቢው 1.69 ዶላር መሆን አለበት።

እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ የዓለም ባንክ ግን 1.90 ዶላር የሚያገኝን ሰው የከፋ ድህነት ውስጥ ይገኛል ሲል ይበይናል።

በቻይና አሁንም በዜጎች መካከል የሰፋ የሃብት ልዩነት ይታያል።